Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጋሸና ግንባር የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የፈፀመው አኩሪ ገድል ሲዘከር ይኖራል – ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋሸና ግንባር የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የፈፀመው አኩሪ ገድል ሲዘከር ይኖራል ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡
ዛሬ በጋሸና ግንባር ለመከላከያ ሰራዊቱ የምስጋና መርሃ ግብር የተዘጋጀ ሲሆን፥ አሸባሪው ህወሓት ለጦርነት ቁልፍ ቦታ የሆነችውን ጋሸናን ለአምስት ወራት በመቆጣጠር በህዝቡ ላይ ሰቆቃዎችን እና ግፎችን ሲፈፅም መቆቱን ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናግረዋል።
ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት በወሰደው የተቀናጀ ጥቃት የሽብር ቡድኑ አከርካሪው ተመቶ ወደ መቀሌ ፈርጥጧል ነው ያሉት።
ዛሬ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ለፈፀመው ገድል ለማመስገን የተገኙት ጀኔራል ብርሃኑ፥ ዕዙ በቀላል መስዋዕትነት የተለያዩ ግዳጆችን በመወጣት በሽብር ቡድኑ ላይ በወሰደው የማጥቃት ዘመቻ በርካታ ምሽጎች ተደምስሰዋል፣ ከእነዚህ ውስጥ የጋሸና እና የሀሙሲት ምሽጎች ይጠቀሳሉ ብለዋል።
ላለፉት አርባ እና ሃምሳ ዓመታት በውሸት የቆየው የሽብር ቡድኑ አሁንም ሽንፈቱን አምኖ ከመቀበል ይልቅ ተመሳሳይ ቅጥፈቱን ዳግም ለትግራይ ህዝብ እየነዛ ይገኛልም ነው ያሉት ጄነራል ብርሃኑ።
ሰላምን አልቀበልም በማለት ተከታታይ ጥቃቶችን በመከላከያ ሰራዊቱ እና በህዝቡ ላይ አስነዋሪ ተግባርን የፈፀመው ቡድኑ፥ የትግራይ ወጣቶችን በማስጨረስ የጭካኔ ተግባሩን አሳይቷል፤ ለዚህ ደግም በየአውደ ውጊያው ለጦርነት ያሰለፋቸው ወጣቶች ወድቀው ቀርተዋል ብለዋል።
ይህ የመጨረሻው ድል አይደለም ያሉት ጄኔራሉ፥ መከላከያ ሰራዊቱ ለኢትዮጵያ አለኝታ ሆኖ ይቀጥላል፤ የህዝቦቿን ሰላምን ያስጠብቃል ሲሉም ገልጸዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፥ “በወራሪው ቡድን ተወረው የነበሩ አብዛኛው የአማራ ክልል አካባቢዎች በእናንተ መስዋዕትነት ነፃ ሆነዋል፤ ለዚህም በእኔ እና በክልሉ ህዝብ ስም ምስጋና አቀርባለሁ” ብለዋል።
“የገጠመን ወራሪ ሃይል ቀላል የሚባል አይደለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በአንድነታችን ላይ በመምጣት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጭፍጨፋ በመፈጸም የጀመረውን ጥፋት ላከሸፈው የመከላከያ ሰራዊት የአማራ ህዝብ ትልቅ ክብር አለው” ነው ያሉት።
በዝግጅቱ ላይ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ጌታቸው ጉዲናን ጨምሮ የዕዙ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ የሃገር የሽማግሌዎች እና አርቲስቶች ተገኝተዋል።
በዕዙ ስር ከጋሳይ፣ጋሸና እስከ ድልብ ድረስ ከፍተኛ ተጋድሎ ለፈፀሙ ለ34ኛ እና 51ኛ ክፍለ ጦር አመራሮች እና አባላት ክብር ይገባቸዋል ተብሏል።
ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመሆን ለተፋለሙት እና ለተዋደቁት የአማራ ልዩ ሐይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ እንዲሁም በደጀንነት ከመከላከያው ጎን ለቆሙት የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ለደቡብ ጎንደር ህዝብ እና አመራር ምስጋና ይገባዋልም ነው ያሉት።

 

በምንይችል አዘዘው
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
 
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
 
መከላከያን ይደግፉ!
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version