Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከተማ አስተዳደሩ በህወሓት የወደሙ የጤና መሰረተ ልማቶችን የሚያደራጅ ግብረሃይል አቋቁሞ እየሰራ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 14 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩ በአማራና አፋር ክልሎች በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ለማስጀመር የተለያዩ ድጋፎች ማድረጉን አስታወቁ።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ የሽብር ቡድኑ በሁለቱ ክልሎች ትምህርት ቤቶችን፣ ጤና ተቋማትን እንዲሁም በተለያዩ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ አካላዊ፣ ስነ ልቦናዊ እና የጤና ችግር ማስከተሉንም አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የህልውና ዘመቻው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዘርፉ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

400 የጤና ባለሙያዎችን ወደ ተለያዩ ግንባሮች መላኩን አስታውሰው፥ በአጠቃላይ ከ75 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ መድኃኒቶች እና የጤና መሳሪያዎችን በመላክ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

በተለይም የሞላሌ፣ የከሚሴ፣ የደጎሎ፣ የደብረሲና፣ የመሀል ሜዳ እና የወረኢሉ ሆስፒታልን በሰው ሀይል እንዲሁም በህክምና መሳሪያዎች እና መድኃኒት አቅርቦት ዳግም እንዲደራጁና ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ማድረግ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም 11 ጤና ጣቢያዎችን የማቋቋም ስራ እያጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመው፥ አስተዳደሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።

ለዚህ እንዲረዳም በከተማዋ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾችና ባለሀብቶች ጋር በመሆን በወደሙ ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት መልሶ በማደራጀት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ግብረ ሀይል ተቋቁሟል ነው ያሉት።

Exit mobile version