አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ የከተማዋን የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ከክፍለ ከተማ አመራሮች እና ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ ያለምንም የፀጥታ ስጋት እንዲስተናገዱ በከተማ አስተዳደሩ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ተቀዳሚ ስራ ነው ተብሏል፡፡
ሰላምና ፀጥታን በማስከበር ተግባር አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ ዕይታን ከፍ ማድረግ እንደሚገባም በውይይቱ ተመላክቷል፡፡
ህዝቡም በዚህ ረገድ ከፀጥታ አካሉ ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰራ ወጥ የሆነ ሕዝባዊ ዝግጅቶች ይደረጋሉ መባሉን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በአዲስ አበባ የፀጥታ ሁኔታ ከማረጋገጥ አኳያ የጥፋት ኃይሎች አዝማሚያን በመመዘን እኩይ አላማን ማክሸፍ እንደሚያሻም በውይይቱ ተጠቁሟል፡፡
ይህን መሰረት ባደረገው የፀጥታው ኃይል ጥረት በርካታ ወንጀሎችን መቆጣጠር መቻሉም ተነስቷል፡፡
እንዲሁም በመታወቂያ አሰጣጥ ዙሪያም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ትእዛዞች መሰረት ያላደረጉ የአሰራር ክፍተቶች መስተዋላቸው ተጠቁሟል፡፡
ህገ ወጥ ግንባታዎችን ተከታትሎ በማፍረስ ረገድ አመርቂ ስራዎች መሰራታቸው የተገለጸ ሲሆን፥ በቅድመ መከላከል ረገድ ግን በርካታ የቤት ስራዎች እንደሚቀሩም ተመላክቷል፡፡
የንግዱ ማኅበረሰብ የትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት መግባታቸውን አስታኮ ከሚያደርገው የዋጋ ጭማሪ ሊታቀብ ይገባልም ነው የተባለው፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

