አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 15 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ዕድል መሰረዙ በሃገር ላይ የተከፈተው የኢኮኖሚ ጠርነት አንዱ ማሳያ ነው አሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል።
ሚኒስትሩ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የዋሺንግተን ውሳኔ ንግድን የፖለቲካ መሳሪያ አድርጎ በመጠቀም ፍላጎቷን ለማስፈጸም የተጓዘችበት ርቀት ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ላይ በግንባር ከተከፈተው ጦርነት በተጨማሪ፥ በዲፕሎማሲው፣ በኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ጦርነት በመክፈት ጫናውን የመክተት ዘመቻ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በእነዚህ ዘርፎች የተከፈቱብንን ጦርነቶች በአንድነት እየመከትን በመምጣታችን በውስጥ ጉዳያችን ለመግባት አሁን ላይ የኢኮኖሚያዊ ጫናው እየጨመረ ይገኛልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
የአሜሪካ መንግስት የወሰደው እርምጃም ኢኮኖሚን የፖለቲካ መሳሪያ አድርጎ ከመጠቀሙም በተጨማሪ የሁለቱን ሃገራት የረጅም ጊዜ ግንኙነት በማበላሸት የአሜሪካን ጥቅም ጭምር የሚጎዳ የተሳሳተ ውሳኔ ነው ብለዋል።
ውሳኔው አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን አቋም በግል ያንጸባረቀችበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ከአጎዋ ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘም ባለፉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ልካ ካገኝችው ዶላር ይልቅ ወደ ሃገር ውስጥ ያስገባቸው ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
ባለፉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ 942 ሚሊየን 218 ሺህ ዶላር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ከውጭ ሃገራት ማስገበቷን ጠቅሰው፥ በአንጻሪ ወደ ውጪ ከተላከ ምርት 350 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥም የአጎዋ ድርሻ 220 ሚሊየን ዶላር ሲሆን 66 በመቶ ይይዛል ነው ያሉት።
በጨርቃ ጨርቅ ረገድም ባለፉት 10 ዓመታት 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ያለቀላቸው የጨርቃ ጨርቅ አልባሳት ወደ ሃገር ውስጥ መግባታቸውን አብራርተዋል።
ለውጭ ገበያ የተላከው ግን 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር መሆኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያ 120 ሚሊየን ህዝብ ያላት ሃገር በመሆኗ የሃገር ውስጥ የገበያ ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በቀጣይ የሃገር ውስጥ ምርት እጠቀማለሁ ነጻነት እጠብቃለሁ በሚል መርህ ለሃገር ውስጥ ምርት እና ገበያ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።
የሃገሪቱ ኢንዱስትሪዎች በአጎዋ ተጠቃሚነት ዕድል ላይ ብቻ ተንጠልጥለው እንዲቀሩ የተስፋፉ ባለመሆኑ ውሳኔው በርካታ አማራጮችን እንድንመለከት ያድርጋል ነው ያሉት።
በአፍሪካ፣ እስያ እና አውሮፓ አማራጭ ገበያዎችን በማፈላለግም ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በበላይ ተስፋዬ
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

