Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላ በጎንደር ለሕዝብ እይታ ሊቀርብ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎንደር ከተማን ቱሪዝም ለማነቃቃትና የቱሪስት ፍሰቱንም ለመጨመር የጥምቀትን በዓል ምክንያት በማድረግ ከ150 ዓመታት የእንግዚዝ ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ለህዝብ እይታ እንደሚቀርብ የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዘውዱ ማለደ አስታወቁ፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ለዳያስፖራው ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ የጥምቀትን በዓል ለማክበር ወደ ከተማው የሚመጡ እንግዶችን በሚስተናገዱበት ሁኔታ በጎንደር ከሆቴል ባለቤቶች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
አቶ ዘውዱ እንደተናገሩት÷ በከተማው የሚከበረው የጥምቀት በዓል የተቀዛቀዘውን የከተማውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ትልቅ ዕድል ይፈጥራል፡፡
የቱሪዝም እንቅስቃሴውንና የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር የአጼ ቴዎድሮስ ሹሩባ (ቁንዳላ) በበዓሉ ወደ ከተማው መጥቶ በሀገር ውስጥና በውጭ ቱሪስቶች እንዲጎበኝ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ቁንዳላው ከበዓሉ ቀደም ብሎ ወደ ከተማው የሚገባበት የክብር አቀባበል ሥነ-ሥርዓት እንደሚከናወን ጠቁመው÷ ይህም ”ትልቅ የሀገር ቅርስና ታላቅ ኩነት ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የከተማው አስተዳደር በዓሉን ለማክበር አንድ ዓቢይና ዘጠኝ ንዑሳን ኮሚቴዎች በማዋቀር ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል።
በበዓሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዳያስፖራዎችና እንግዶች ወደ ከተማው ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
የከተማውን ሰላምና የእንግዶችን ደህንነት ለማስጠበቅ የከተማው ነዋሪዎችና ወጣቶች የሚሳተፉበት የፀጥታ አደረጃጃት መዋቀሩንም አቶ ዘውዱ ገልጸዋል፡፡
በከተማው በሆቴልና ቱሪዝም ስራ የተሰማሩ የንግድ ድርጅቶ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉና እንግዶቹን በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እንግዳ አክባሪነት ተቀብለው እንዲያስተናግዱ አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ጣሂር መሐመድ በበኩላቸው÷ በክልሉ የገናና የጥምቀት በዓላትን በላሊበላና በጎንደር ከተሞች በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት የደረሰበት የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ በፍጥነት ጥገና ተደርጎለት በዓሉን ለሚያከብሩ ምዕመናንና ዳያስፖራዎች እንዲያስተናግድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ሆቴሎችና የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ባለማድረግ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version