Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተከፈተብንን የኢኮኖሚ ጦርነት በድል አድራጊነት ለመወጣት ዘመናዊ የግብርና ስርአት መዘርጋት ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) የተከፈተብንን የኢኮኖሚ ጦርነት በድል አድራጊነት ለመወጣት ዘመናዊ የግብርና ስርአት መዘርጋት እንደሚገባ ተመላከተ።

በደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ የገጠር መሬት አስተዳደር መረጃ ስርአት ግንባታ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሔደ ነው፡፡

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር÷ አሸባሪው ህወሀት ሀገርን ለማፍረስ በወጠነው እኩይ ሴራ ለበርካታ ዜጎች ሞት ፣ስደት ፣የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

የሽብር ቡድኑን ድርጊት ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ ቆመው ጠላትን ድል ማድረግ መቻላቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጠላት ሌላው ሴራ የኢኮኖሚ ጦርነት ነው ያሉት አቶ ኡስማን ይህንን በአስተማማኝ ደረጃ ለመመከት ደግሞ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ስርአትን በመዘርጋት ምርታማነትም ማሳደግ ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።

የኢኮኖሚ ጦርነትን ከምንዋጋባቸው አውደ ውጊያዎች ውስጥ አንዱ መሬትን በአግባቡ መጠቀም እና ማስተዳደር ዋነኛው መሰረት ነው ብለዋለሸ።

ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና የህዝቦችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የዘመነ የመሬት አስተዳደር ስርአት ወሳኝ መሆኑንም አቶ ኡስማን በአጽንኦት ተናግረዋል።

በክልሉ ከ1997 ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው የ1ኛ ደረጃ የመሬት የይዞታ ማረጋገጫ እንዲሁም ከ2003 ጀምሮ ደግሞ የ2ኛ ደረጃ የመሬት የይዞታ ማረጋገጫ ስራ በትኩረት መሰራቱን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም ባልተገባ መንገድ ሲፈጸም የነበረው የመሬት አስተዳደርን በመረጃ በማበልጸግ ህብረተሰቡ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን አቶ ኡስማን አብራርተዋል።

አመራሩ የመሬትን ፋይዳ ተገንዝቦ በመሬት መረጃ አያያዝ እና አስተዳደር ዘርፍ ላይ ያሉ ችግሮችን መፍታት ይገባልም ነው ያሉት።

የተጀመረው ሀገራዊ የልማት ግብ ሊሳካ የሚችለው በዘመናዊ የመሬት አጠቃቀም እና አስተዳደር ስርአት ነው ያሉት አቶ ኡስማን በአጭር ጊዜ ከድህነት መውጣት እንድንችል በቁጭት መስራት ይገባል ሲሉም መናገራቸዉን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version