Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአር ቲ ዘጋቢ በህወሃት ታጣቂዎች ከተደፈሩት የ80 ዓመት አዛውንት ጀምሮ እስከንብረት ዝርፊያና ውድመት ድረስ ለዓለም አሳይታለች

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአር ቲ ዘጋቢ በደብረ ብርሃን ሆስፒታል በመገኘት የህወሃት አሸባሪ ቡድን ታጣቂዎችን ዘግናኝ የአስገድዶ መድፈርና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያካተቱ ወንጀሎችን ቀጥታ ለዓለም አሳይታለች።

የደብረ ብርሃን ኮምፕሬንሲቭ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዳግም ሺመላሽ ለዘጋቢዋ እንደተናገረው፥ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሰለባ የሆኑ 25 ሴቶችን ሆስፒታሉ ተቀብሎ አክሟል።

ከእነዚህ ሴቶች መካከል አስሩ አሁንም ህክምና እየተከታተሉ መሆናቸውን እና ከእነዚህ ውስጥም የ80 ዓመት አዛውንት ሴት እንደሚገኙ አመልክቷል።

የ80 ዓመት አዛውንቷ ለጋዜጠኛዋ የህወሃት ታጣቂዎች እንዴት ወደቤታቸው መጥተው እንደደፈሯቸው ገልፀውላታል።

ሲያስረዷትም “ምሽት አራት ሰዓት ላይ መጥተው በራፌን አንኳኩ፤ የቤቴን በራፍ እንድከፍት ጠየቀኝ፤ ስከፍት በቡጢ አለኝ፤ ወደኩኝ፤ ደፈረኝ፤ መሳሪያ የያዘ አዲስ ሰው ነው፤ ምን እንደፈፀመብኝ በፍጹም አልረሳም” ብለዋታል።

ሌላኛዋ ታካሚ ሴት በአራት ታጣቂዎች ተራ በተራ መደፈሯን አስረድታለች።

ጋዜጠኛዋ በህወሃት ታጣቂዎች ተይዛ ወደነበረችው ሸዋሮቢት በማቅናት የሽብር ቡድኑ የግለሰቦችን መኖሪያ ቤት ምን ያህል ዘርፎና አውድሞ መሄዱን በምስል አስደግፋ አቅርባለች።

 

ሙሉ ዘገባውን ለማየት ሊንኩን ይጫኑ

 

Exit mobile version