Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ወደ አፋር ክልል ለሚመጡ ዳያስፖራዎች ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል-የአፋር ክልል መንግሥት

 አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ወደ አፋር ክልል ለሚመጡ ዳያስፖራዎች ሰፊ ዝግጅት መደረጉን የአፋር ክልል መንግሥት አስታውቋል፡፡

የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ አብዱልቃድር በሰጡት መግለጫ፥ ዳያስፖራዎች ወደ ክልሉ ሲመጡ ደማቅ አቀባበል ለማድረግና በቆይታቸውም ሊታዩና ሊሰሩ የታሰቡ ስራዎችን በማስጎብኘት የተሳካ ጊዜ እንዲያሳልፍ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ጎብኚዎች በክልሉ በአሸባሪው ህወሃት ቡድን ከፍተኛ ጉዳት የደረሳባቸውን ስፍራዎችና የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ኮሚቴ ተዋቅሮ ስራ መጀመሩንም ነው የተናገሩት፡፡
በዚህም በአሸባሪው ህወሓት ከ109 በላይ ህፃናት የተገደሉበት የ”ጋሊኮማ ጅምላ ጭፍጨፋ”ን እንደ አንድ መዳረሻ በመውሰድ ዳያስፖራው ስለ ክስተቱ የተገነዘበውን ሃቅ ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ እንዲያሳውቅ ይደረጋል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ በጭፍራ እና ካሳጊታ ያስከተለው ውድመትም የጎብኚዎች ሌላኛው ትኩረት እንዲሆን መታሰቡን የገለፁት ኃላፊው፥ ዳያስፖራው በመልሶ ግንባታ ስራው በመሳተፍ የሽብር ቡድኑ በህዝብ ላይ ያደረሰውን ምስቅልቅል ማቃለል እንዲችል ይደረጋልም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ጎብኚዎች የአፋር ክልል መዲና ሰመራ ከተማን ማዕከል በማድረግ 5 የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲመለከቱ በማድረግ ለኢንቨስትመንት ክፍት የሆኑ ዕድሎችን ለማስተዋወቅም ታቅዷል፡፡
ከእነዚህም የአዋሽ ወንዝ የሚሰርግበትና የአዞ ሃብት ያለበትን የ”አፋምቦ ሃይቅ” ዳያስፖራው ማህበረሰብ በኢንቨስትመንት እንዲሰማራ ምቹ ሁኔታዎችን የያዘ ስፍራ በመሆኑ ከተለዩት መዳረሻዎች መካከል አንደኛው መሆኑን ክልሉ ገልጿል፡፡
የሃገሪቱን 80 በመቶ የጨው አቅርቦት የያዘው የ”አፍዴራ ሃይቅ” ሌላኛው አማራጭ የቱሪስት መቆያ ሲሆን፥ ጎብኚዎች የተሳካ ጊዜ እንደያሳልፉበት ዝግጁ ተደርጓል፡፡
ዳሎል ሌላኛው መዳረሻ ነው፤ ይህ ስፍራ የግመሎች ጉዞ “ቅፍለት” የሚከናወንበት እንዲሁም በተለያዩ ህብረቀለማት ያሸበረቁ ማዕድናት ያሉበት ነው፡፡
በኤርታሌ እሳተ-ገሞራም ለዳያስፖራው የተለያዩ የምሽት ፕሮግራሞች ተዘጋጅተዋል የተባሉ ሲሆን፥ አላሎባድ ፍልውሃ ክልሉ ካሉት ውብ የቱሪስት መዳረሻዎች ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሃገር ቤት መምጣት ለጀመሩ ዳያስፖራዎች ምስጋና ያቀረበው የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሰው ዘር መገኛ ወደሆነችው አፋር ክልል እንኳን ደህና መጣችሁ “ኡንካዕ ማዑክ ተሜቴንም” ብለዋል፡፡
ዲያስፖራው ቆይታው ውጤታማ እንዲሆንም የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከሚመለከተው የፀጥታ መዋቅሮች ጋር በመሆን ሰፊ ዝግጅት ማድረጉንና ህብረተሰቡም በፈጣኑ የአፋር የመረጃ ስርዓት-ዳጉ በኩል የዳያስፖራው ጠባቂ እንዲሆን ግንዛቤ መፈጠሩን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
በሶዶ ለማ
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version