አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና ብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት በጋራ የሚያከናውኑት የብሄራዊ መታወቂያ ምዝገባ የጋራ ፕሮጀክት በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በይፋ ተጀምሯል።
የሙከራ ፕሮጀክቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ሳንዶካን ደበበ ባስጀመሩበት ወቅት፥ የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ለውጡ ይዞት የመጣው እና እንደ ሀገር ብዙ ያልተሰራበት ጠቃሚ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ከደህንነት፣ ከባንክ ሲስተም፣ ከህግ ትግበራ፣ ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲሁም ከሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ጋር የሚገናኝና ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የጠቆሙት አቶ ሳንዶካን፥ የሙከራ ፕሮጀክቱ ውጤታማነት ተገምግሞ ወደ ሌሎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራው እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ዮዳሄ አርአያስላሴ በበኩላቸው÷ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኙ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎችን በአንድ ቦታ ለማግኘት ስለሚያስችል እና የዜጎቹንም የተመዘገበ መረጃ ወደ ብሄራዊ የመረጃ ቋት ለማስገባት ጠቃሚ በመሆኑ ፓርኩ የሙከራ ፕሮጀክቱን ለመተግበር ጥሩ አማራጭ ነው ብለዋል፡፡
ፓርኩ የሰራተኞቹን መረጃ እንዲያውቅ፣ አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርግ እንዲሁም ከደህንነት አኳያ ብዙ ጥቅሞች ያሉት ፕሮጀክት እንደሆነ መናገራቸውን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከ20 ሺህ በላይ ሰራተኞች በሚገኙበት በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተጀመረው የብሄራዊ መታወቂያ የሙከራ ፕሮጀክት ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሁሉንም ሰራተኞች የመመዝገብ ስራው እንደሚከናወን ተገልጿል።
የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ስር ሆኖ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን÷ እስከ 2018 ባለው ጊዜ ውስጥ እስከ 70 ሚሊየን የሚደርሱ የኢትዮጵያ እና የውጪ ሀገር ዜጎች ዲጂታል መታወቂያ ወይም ልዩ መለያ ኮድ እንዲኖራቸው ይሰራል ተብሏል።

