Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተለየ ሐሳብ ያለው ኢትዮጵያዊ ሐሳቡን የሚቀበል ሥርዓት አጥቶ ጫካ የሚገባበት ጊዜ መቆም አለበት- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለየ ሐሳብ ያለው ኢትዮጵያዊ ሐሳቡን የሚቀበል ሥርዓት አጥቶ ጫካ የሚገባበት ጊዜ መቆም እንዳለበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናገሩ፡፡
 
ሀገር የሐሳብ ስሪት ውጤት ናት፤ የተለያዩ ሐሳቦች ሕብር ፈጥረው የሚገነቧት ሀገር በምጣኔ ሃብት፣ በፖለቲካ እና በማኅበራዊ ውቅሯ ጠንካራ ናት ይላሉ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፡፡
 
ነፍጥ ካነገቡት በላይ የሐሳብ ልዩነትን ተቀብለው እና አስማምተው ሀገር ያቆሙት የተሻለ ለውጥ አምጥተዋል፤ የተለየ እና የተለያየ ሐሳብ መያዝ እና ማንጸባረቅ በራሱ ችግር አይደለም፤ ችግር የሚሆነው ግን የሐሳብ ልዩነት ወደ ግጭት ሲያመራ እና ዋጋ ሲያስከፍል ነው፤ ኢትዮጵያ ለዘመናት በዚህ ብዙ ዋጋ ከፍላለች ነው ያሉት፡፡
 
ጥንታዊ ግሪካዊያን አርዮስ ፋጎስ የሚባል የሐሳብ አደባባይ ነበራቸው፤ ሰው ስለሀገሩ እና በሀገሩ የተለየ ሐሳብና እሳቤ ሲኖረው ሐሳቡን ከሌሎች ጋር የሚያንሸራሽርበት በኢትዮጵያም እንደ ጎንደር ጉባኤ አይነት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ልዩነቶች በልሂቃን የሚሞገቱባቸው አደባባዮች እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል ብለዋል፡፡
 
ጥንት ኢትዮጵያዊያን ፍትሕን አዋቂ ብቻ ሳይሆኑ ስለፍትሕ ሲሉ ራሳቸውን የገዙ እና ለሌሎች ሐሳብ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጡም እንደነበሩ ይነገራሉ፡፡
 
የቱ ላይ እንደተቆረጠ በውል ባይታወቅም በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ፖለቲካ ውስጥ የሐሳብ ልዩነት ከአደባባይ ማስታረቅ ይልቅ ለግጭት እና ለልዩነት የቀረበ እንደነበር ተደጋግሞ ታይቷል፤ የተለየ ሐሳብ ያላቸው ዜጎች የልዩነት ሐሳባቸውን የሚቀበል እና በአግባቡ የሚያስተናግድ ሥርዓት በማጣታቸው ብቻ በርካቶች ጫካ፣ ውስኖች ወህኒ እና አብዛኛው ደግሞ ከሀገሩ ተገፍቶ በውጭ እንዲያሳልፍ ተገዶ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
 
በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ የሚስተዋሉትን ልዩነቶች ለማጥበብ እና ሀገራዊ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ባለፉት ዘመናት አካታች ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር እንዲደረግ ሲጠየቅ መቆየቱን ጠቁመው በሽብር ቡድኑ ትህነግ መራሹ መንግሥት ዘመን የሐሳብ ልዩነትን በምክክር ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ግጭቶችን በመጥመቅ የሚያተርፉ ኃይሎች ጥያቄዎችን ሲገፉት ቢቆይም ጊዜው ሲደርስ በቅርቡ እውን ለመሆን በቅቷል ይላሉ፡፡
የለውጡ የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች ብሔራዊ የምክክር መድረኩ እንዲደረግ ሲጠየቁ መቆየታቸውን ያወሱት አማካሪው ሂደት እና ዝግጅት ያስፈልገው ስለነበር እስከዚህ ጊዜ ድረስ ቢቆይም ተቋማዊ ሆኖ በኮሚሽን ደረጃ መዋቀሩ በመልካምነት የሚታይ ነው ፡፡
 
በበርካታ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ እይታዎች እና አረዳዶች አሉ የሚሉት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጉዳዮቹን ወደ ጠረንጴዛ በማምጣት መመካከር እና የጋራ አስተሳሰብ መፍጠር አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡
 
በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ፖለቲካ ሂደት ልዩነቶች ከጫካ ወደ አደባባይ ተሸጋግረዋል፤ከዚህ የተሻለው ደግሞ የተለየ ሐሳብ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ልዩነታቸውን ይዘው በጠረጴዛ ዙሪያ መምከር መቻላቸው የተሻለ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
ብሔራዊ የምክክር መድረኩ ከወቅቱ ጦርነት ጋር ተያይዞ ድርድር የሚል እንደምታ ይዟልና ግንኙነት ይኖረው ይሆን በሚል አሚኮ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ሲመልሱ አሸባሪው ትህነግ በተፈጥሮው መመካከር እንደማይወድ ገልጸው የኮሚሽኑ መቋቋም ለእንደራሴዎች የቀረበበት ወቅት ከአሸባሪው ቡድን ሽንፈት ጋር በተመሳሳይ ወቅት በመቅረቡ የተፈጠረ ነው በመሆኑ እንጅ ብሔራዊ ምክክሩ ድርድር ከሚባለው ጉዳይ ግንኙነት የለውም ብለዋል።
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version