አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ40 ዓመት በላይ አሜሪካን ሀገር የኖሩት አቶ ሚደቅሳ በየነ የኢንተርኔት ግንኙነት በሌለበት ቦታ የዲጂታል ትምህርት መስጠት የሚያስችል መሳሪያ ለሙከራ ለሀገራቸው ይዘው መጥዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ሀገር ቤት መመለስ ጥሪን ተቀብለው ወደ ሀገራቸው የመጡ ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ ሚደቅሳ ወደ ሀገር ሲመጡ የኢንተርኔት ግንኙነት የሌላቸው ትምህርት ቤቶችን ሊጠቅም የሚችል ቴክኖሎጂ ይዘው እንደመጡ ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂው በሶላር ኃይል የሚሰራ፣ የራሱ ዋይፋይ ያለውና ተንቀሳቃሽ 2 ቴራባይት ሰርቨር የያዘ ሲሆን÷ከኮምፒውተርና ከሞባይል ጋር በማገናኘት የመማሪያ መሳሪያዎችን ማግኘት የሚቻልበት ነው ተብሏል።
ቴክኖሎጂው የተለያዩ የትምህርት አይነቶች የያዙ መጽሐፍት፣ መርጃ መጽሐፍት፣ ሌክቸሮች እና ቪዲዮዎች፣ ጥናታዊ ጽሑፎች፣ ንግግሮች፣ መዝናኛዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ማስረጃዎችንም የሚይዝ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከ60 ሺ በላይ መጽሐፍትን የያዘው ስርዓቱ መጽሐፍቶቹን በማንኛውም ጊዜ በነፃ ማውረድም የሚስችል ነው መባሉንም ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአሁን ሰዓት መሳሪያውን በሀገር ውስጥ ለመጠቀም እንዲቻል የትምህርት ሚኒስቴር የአይሲቲ ባለሙያዎች እንዲገመግሙት እየተደረገ ነው።
ባለሙያዎቹ ሲስተሙ ላይ የሀገር ውስጥ የትምህርት አይነቶችን በመጫን ሀገርኛ ይዘት እንዲኖረው የማድረግ ስራዎችን እንደሚሰሩም ተገልጿል።
በቀጣይ የዚህ ቴክኖሎጂ ውጤታማነት ተገምግሞ ቀጣይ ስራዎች እንደሚሰሩ ተመላክቷል፡፡
ሌሎች ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ወደ ሀገር ሲመጡ የትምህርት ስርዓቱን ሊያግዝ የሚችል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

