አዲስ አበባ፣ታህሳስ 22፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የተጎዱ ቅርሶችን ወደ ነበሩበት በፍጥነት በመመለስ የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃት እንደሚገባ የቱሪዘም እና የቅርስ ባለሙያዎች ተናገሩ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስለጣን ከፍተኛ የቅርስ ባለሙያ አቶ ጌዲዮን ሽመልሽ እንደተናገሩት፥ አሸባሪው ህዋሃት በወረራ ይዟቸው በነበሩ የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎች በቅርሶች፣ በአብያተ ክርሰቲያናት ፣ በመስጊዶች፣ በብሄራዊ ፓርኮች እና በጥብቅ ደኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው ህወሃት ከጦርነት ህግ ውጪ የአምለኮ ስፍራዎችን መሸሸገያ ማድረጉን እና ብሄራዊ ፓርኮችና ጥብቅ ደኖችን የውጊያ ቀጠና በማድረግ በውስጣቸው ያሉት አዕዋፍት እና እንስሳት እንዲሰደዱ እና እንዲጠፉ ማድረጉን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
የቅርስ ጉዳት በገንዘብ አይገለጽም ያሉት ባለሙያው፥ በጦርነት የተጎዱ ቅርሶችን በመለየት ወደ ነበሩበት ለመመለስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ዳይሬክትር አቶ ሙሳ ከድር በበኩላቸው፥ የቱሪዝም ዘርፉ ጦርነት ከመከሰቱ በፊት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቀዛቅዞ እንደነበር አስታውሰው፥ በተከሰተው ጦርነት እና አሸባሪው የህወሃት ቡድን በቅርሶች ላይ ባደረሰው ጉዳት ምክንያት ዘርፉ የበለጠ መቀዛቀዝ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
ባለሙያው ከቱሪዝም ሚኒስቴር አጥኚ ቡድን ወረራ በተፈጸመባቸው አከባቢዎች ምልከታ ማድረጉን የገለጹ ሲሆን፥ ከማህበረሰባዊ ጉዳት በተጨማሪ የቅርሶችን እሴት በማጥፋት በእምነት ቦታዎች እና በቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ ቡድኑ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በጦርነቱ በነበረው የተኩስ ልውውጥ ቅርሶች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ጉዳት እንደደረሰባቸው ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
ስለሆነም የተጎዱ ቅርሶችን እና የቱሪዝም መዳረሻዎችን ወደ ነበሩበት በመመለስ የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃት እንደሚገባ ባለሙያው አመላክተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

