አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ምክንያት ከጥቅምት 8 እስከ ታህሳስ 11 ቀን 2014 ዓ.ም አገልግሎት አቋርጦ የነበረው የሀይቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ወደ ሙሉ መደበኛ አገልግሎት ለመግባት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡
አሸባሪው እና ዘራፊው የህወሓት ቡድን በሆስፒታሉ ላይ ባደረሰው ዘረፋና ውድመት የተቋሙን ግንባታ ሳይጨምር በህክምና ቁሳቁሶች ላይ ብቻ 44 ሚሊየን ብር የሚገመት ጥፋት አድርሷል፡፡
በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሙሉ ኃላፊነቱን በመውሰድ እና ግብአቶችን በማሟላት ታህሳስ 12 የጤና ተቋሙ በከፊል ስራ እንዲጀምር አድርጓል።
በአሁኑ ወቅትም የታካሚዎች ቁጥር ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ሲሆን፥ ሆስፒታሉ የሪፈር አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸው ታማሚዎች ከደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የሀይቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግማሽ ሚሊየን ለሚደርሱ ሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው።
አሁን ላይ ሆስፒታሉ የተመላላሽ፣ ድንገተኛ ህክምና፣ ወሊድ፣ የቅድመ ወሊድ አገልግሎት፣ የፕሮግራም መድኃኒት አገልግሎት እና ተኝቶ ለሚታከም አገልገሎት እየሰጠ መሆኑን የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያ አቶ ሀሚድ ሁሴን ተናግረዋል።
በቀጣይም የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሉ ወደ መደበኛ ሙሉ አገልግሎት እንዲገባ ለማድረግ በከባድ መሳሪያዎች የፈረሱ ግንባታዎችን የመጠገን እና አስፈላጊ የህክምና ግብአቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በለይኩን አለም
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

