አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ፡፡
የደቡብ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ሲያካሔዱት የነበረው የውይይት መድረክ ተጠናቋል፡፡
የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት እና ሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኸይረዲን ረዲ የተካሄደውን ውይይት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በድህረ ጦርነት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ ከስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ የአካባቢን ሰላም ማስጠበቅ፣ ሊያጋጥም የሚችለውን ኢኮኖሚ ችግር እንዲያንሰራራ ማድረግ፣ የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት ለማጎልበት በትኩረት መሰራት እንዳለበት የጋራ አቋም መያዙን አብራርተዋል።
መንግስት የዜጎችን እና የሀገርን ደህንነት ለማስጠበቅ ተገዶ ወደ ጦርነት መግባቱን ያወሱት አቶ ኸይረዲን ዘመቻ ለኅብረ ብሄራዊ አንድነት የመጀመሪያ ምዕራፍ በድል ቢጠናቅቅም በቀሪ ጊዜያት ከድህረ ጦርነት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት ላይ ይተኮራል ብለዋል።
በጦርነቱ የውስጥ እና የውጭ ተዋንያን መኖራቸውን ያወሱት አቶ ኸይረዲን ሀገራዊ አንድነትን ይበልጥ በማጠናከር ለላቀ ስኬት መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የክልሉ ህዝብ የህልውና ዘመቻው ስኬታማ እንዲሆን የገንዘብ የአይነት እና የሰው ሀይል ድጋፍ በማድረግ ረገድ ላደረገው የላቀ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በድህረ ጦርነት ጥላቻን በማስወገድ እና የትብብር መንፈስ በማጠናከር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት በሚያስችሉ ነጥቦች ላይ ከስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።
በህልውና ዘመቻው የታየውን አንድነት በማስጠበቅ ልማታችንን ማስቀጠል ይገባልም ሲሉ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል እንደ ደቡብ ክልል ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መፍታት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል ሲሉም አስረድተዋል።
የአርሶ እና አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የልማት ተጠቃሚነት ማሳደግ የገቢ አሰባሰብ አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ አቶ ኸይረዲን በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
በጦርነቱ ቀጥተኛ ተጎጂ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ ማቋቋም እና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መገንባት እንደሚገባም በውይይት መድረኩ የጋራ አቋም መያዙን አብራርተዋል ከደቡብ ከልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

