አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት የተደቀነባትን ጫና በአሸናፊነት እንድትወጣ በቀዳሚነት መታሰብ ያለበት ኢኮኖሚውን የሚደግፍ የንግድ ስርዓት ማበጀት መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ።
የሀገር ውስጥ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ለገበያ በመጠቀም ኢኮኖሚውን መታደግ እንደሚቻል ተደጋግሞም ይነሳል።
ሀገሪቱ ላይ ከውስጥ እና ከውጭ የተቃጣውን ጥፋት በትክክል የተረዳው የዳያስፖራው ማህበረሰብ ስለ ሃገሩ እየሞገተ በሃገር ፍቅርና ተቆርቋሪነት ለሌሎች ምሳሌ በሚሆን መልኩ እየታገለና ታሪክ እየሰራ ይገኛል።
የዳያስፖራው አቅም ግን በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ እና እድገት ላይ ያለው ሚና የጎላ በመሆኑ ምቹ አሰራሮችን የመዘርጋት ቀጣይ እቅድ ከወዲሁ ሊዘጋጅ እንደሚገባው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤቶች ዋና ጸሃፊ አቶ ክቡር ገና ይናገራሉ።
የዲያስፖራው ለሃገር ሁለንተናዊ እድገት ያለው አስተዋጽኦ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።
ጉዳዩ የሀገርን ችግር በአጭር ጊዜ ሊደግፉ እና የኢኮኖሚውን ጥያቄ ሊመልሱ የሚችሉ የልማት ስራዎችን ለይቶ ማሳተፍ ቀዳሚው ሊሆን እንደሚገባ አቶ ክቡር ገና ያነሳሉ።
በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳቡን የጠየቅነው የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዳያስፖራው ባልተነካው የወጪ ንግድ እንዲሳተፍ ይመክራል።
የገበያ እድል ያለገኙ ብዙ የሀገር ውስጥ ምርቶች በመኖራቸው ዳያስፖራው በዚህ ላይ እራሱንም ሃገርንም የሚደግፍበት ዘርፍ እንደሆነ የሚገልጹት በሚኒስቴሩ የንግድ ስርዓት እና ድርድር ባለሙያ አቶ ሙሴ ምንዳዬ ናቸው።
የሃገር ውስጥ ምርትን በሰፊው የማስተዋወቅ ተግባርንም ሌላው የዲያስፖራውን ተሳትፎ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም ስኬት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከነበረው አሰራር በተለየ ከቢሮክራሲ የፀዳ አሰራር እየዘረጋ መሆኑን አንስተው፥ ይህም አሰራር በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ነው የጠቆሙት።
በፍሬህይወት ሰፊው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!