አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰራዊቱ የጀግንነት ተጋድሎ የገጠሙንን ውስብስብ አገራዊ አደጋዎች መመከት ችለናል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አቅራቢነት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ ለ101 የአገር መከላከያ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የማዕረግ እድገት ሰጥተዋል፡፡
በዚህም የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ የፊልድ ማርሻል ማእረግተኛ በመሆን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ሆነዋል።
ለሌሎች ከፍተኛ የመከላከያ የጦር መኮንኖች ማእረግ የተሰጣቸው ሲሆን፤ በዚህም መሰረት 4 የሙሉ ጀነራል ማእረግ፣ 14 የሌተናል ጀነራል ማእረግ፣ 24 የሜጀር ጀነራል ማእረግ እና 58 የብርጋዴር ጀነራል ማእረግ ተሰጥቷል።
ጀኔራል አበባው ታደሰ፤ ጀነራል ባጫ ደበሌ፤ጀነራል ሀሰን ኢብራሂም እና ጀነራል ጌታቸው ጉዲና የሙሉ ጀነራል ማዕረግተኛ ሆነዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በሰራዊቱ የጀግንነት ተጋድሎ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ውስብስብ አገራዊ አደጋ መመከት ተችሏል ያሉ ሲሆን÷ በዚህም ገድል ከነበሩ ችግሮች መሻገር ችለናል፤ በቀጣይም ለኢትዮጵያ እድገትና ሰላም ይበልጥ መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡
ሰራዊቱ ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ ለከፈለው መስዋትነትም የላቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን የሚያስጠብቅላት ዘመናዊ ጦር እየገነባች መሆኑን ጠቅሰው፥ ዜጎች “ሰራዊቱ የኔ ነው” በሚል እሳቤ ደጀንነታቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፊልድ ማርሻል ማእረግተኛ ብርሃኑ ጁላ፤ የማዕረግ እድገቱን ያገኙት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ውጊያ በመምራት፤ ኃይል በመገንባትና በጀግንነት ድል ያስመዘገቡ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ናቸው ብለዋል፡፡
የማእረግ እድገቱ በሰራዊቱ ዘንድ የኃይልና የሞራል የበላይነት ለመገንባት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የማእረግ እድገት ካገኙ ከፍተኛ መኮንኖች መካከል ጀነራል ባጫ ደበሌና ብርጋዴር ጀነራል ሁሉአገርሽ ድረስ የማእረግ እድገቱ ሰራዊቱ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ ከፍተኛ የሞራል መነሳሳት እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን ህዝብ ለማገልገል ተጨማሪ አደራ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

