Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መንግስት አካባቢውን ከአሸባሪው ሸኔ ነጻ በማድረግ ወደ ቀያችን እንዲመልሰን እንፈልጋለን – ተፈናቃዮች

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አስቸኳይ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ያስፈልገናል ሲሉ በአሸባሪው ሸኔ ጥቃት ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ተናገሩ።
 
ከምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ በሸኔ ጥቃት የተፈናቀሉ ዜጎች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ተወልደው ባደጉበት አካባቢ በአሸባሪው ሸኔ ሀብት ንብረታቸው ተዘርፎ እና ንጹሃን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለው አካባቢያቸውን እንደለቀቁ ተናግረዋል፡፡
 
ደብረብርሃን ከተማ ከገባን ጊዜ ጀምሮ መንግስትና በጎ አድራጊ ግለሰቦች ተቀብለው ለማስተናገድ ያደረጉት ጥረት መልካም ነው ያሉት ተጎጂዎቹ÷ ነገር ግን ተፈናቃዩ ከፍተኛ በመሆኑ የዕለት ምግብና የአልባሳት ድጋፍ በተገቢው መንገድ ሊደረግልን ይገባል ብለዋል።
 
ከጊዜያዊ ድጋፉ ባለፈም አካባቢውን ከአሸባሪ ቡድኑ ነፃ በማድረግ በዘላቂነት ሰላም ተከብሮ ወደቀያቸው መንግስት እዲመልሳቸው ጠይቀዋል።
 
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበባው መሰለ÷ አሁን ላይ ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሸኔ የሚያደርሰውን ግፍና በደል ሸሽተው የመጡ ከ25 ሺህ በላይ ዜጎች በደብር ብርሃን ከተማ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
 
በሌላ በኩል በዞኑ በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ጥቃት ምክንያት የተፈናቀሉ ከ1 ሚሊየን 53 ሺህ በላይ ዜጎች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡
 
ያለውን ጫና በመቋቋም ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ለመጡ ተጎጂዎችም ለማገዝ ጥረት ቢደረግም አሁንም በየቀኑ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢው እየገቡ በመሆኑ በተፈናቃዮች ችግር ልክ ለማገዝ ተቸግረናል ነው ያሉት።
 
ለነዚህም ተጎጂዎች በመንግስት በኩል ድጋፍ እንዲደረግ በመዋቅራቸው በኩል ለክልልና ለፌደራል መንግስቱ ማሳወቃቸውን የገለፁት አቶ አበባው÷ በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ተጎጂዎችን እዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።
 
በአበበ የሸዋልዑል
Exit mobile version