አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ-ጣሊያን ትብብር ፕሮጀክት በአግሮ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የውጪ ምንዛሪ ለሀገሪቷ ለማስገኘት እንደሚሰራ ተገለጸ፡፡
አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር በማስተሳሰር የተሻለ የሥራ ሥምሪት እና የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል፡፡
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የአጋርነትና ፈንድ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጥዑመ-ዝጊ በርሄ ÷ የኢትዮ – ጣሊያን ትብብር ፕሮጀክት ለትግበራ የሚረዳውን ዓመታዊ ዕቅድ እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል፡፡
ዓላማውም ውጤታማ የቅድመ ሥራ ስምሪት አገልግሎት (PES) በመገንባት የገጠሩን ኅብረተሰብ እና ሥራ ፈላጊ ወጣቶችን በሥራ ገበያው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነው ተብሏል፡፡
ለዚህም አማካይ የሥራ ማስታወቂያ ድርጅቶችን (LMIS) በመደገፍ ለሥራ ፈላጊዎች አገልግሎት የሚሰጡ ፓይለት የገጠር ሥራ ማዕከላትን እንደሚያጠናክሩ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮ -ጣሊያን ትብብር ፕሮጀክት በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ሲዳማ ክልሎች ይተገበራልም ነው የተባለው፡፡
ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነትም በኢጣሊያ መንግስት በኩል የ 4 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ተደርጎ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተነግሯል፡፡
የኢጣሊያ የልማት ትብብር÷ የሚተገበሩትን የልማት ፕሮጀክቶችን የመለየት ፣የማዘጋጀት እና በገንዘብ የመደገፍ ብሎም የመከታተል ሥራ ይኖረዋልም ነው የተባለው፡፡
የኢትዮጵያ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ ክልሎቹና ብሔራዊ ባንክ የራሳቸው ኃላፊነትና በፕሮጀክቱ የተወሰነ ተግባር እንዳላቸውም ተገልጿል፡፡
በዚህ የፕሮጀክት ትግበራ የምክክር ውይይት ላይ የቡሬ ፣የይርጋለም፣ የቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ከላይ የተጠቀሱት ሦስት ክልሎች መነሻ ሰነድ መቅረቡን ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

