Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዳያስፖራዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈስሱ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳያስፖራዎች በአግሮ ፕሮሰሲንግ ፣ በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈስሱ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳኅሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለዳያስፖራ አባላት የቤተሰብ እራት እና የምስጋና ዝግጅት አቅርቧል።
በምስጋና እና በቤተሰብ እራት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተርድረስ ሳኅሉ ፥ የገጠምነው ጠላት አሸባሪውን ቡድን ብቻ አይይለም፤ የውስጥ ተላላኪ ባንዳዎች እና ከውጭ ጠላቶች ጋር ነው ብለዋል።
የአንዳንድ ምዕራባውያን የዲፕሎማሲ ጫና ሌላኛው ጦርነት እንደነበር ገልፀዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ ጫናዎችን በመቋቋም ከሕዝብ ጋር ሆኖ ትግል ሲያደርግ እንደነበርም ተናግረዋል።
የዳያስፖራ አባላትም የአንዳንድ ምዕራባውያን ጫናን እንዲቀንስ፣ የውሸት ፕሮፖጋንዳቸውን በማጋለጥ እና የኢትዮጵያን እውነት በማሳየት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል ነው ያሉት።
የተገኘው ድል ጊዜያዊ ድል ነው ያሉት ዶክተር ድረስ ፥ቀጣይ የምንሠራቸው ሥራዎች ይቀሩናል፣ አሁን ላይ ለተገኘው ድል ግን የዳያስፖራው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለነበር ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።
የቤተሰብ የእራት ግብዣው ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ዳያስፖራዎችን ለማስተዋወቅና ለማገናኘት፣ እርስ በርስ እንዲወያዩ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
የዳያስፖራ አባላት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን በማየት የተጎዱ ወገኖችን በመጠየቅ ማፅናናት እና መልሶ በማቋቋም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል። በጦርነቱ የተጎዳውን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዳያስፖራው በከተማዋ ቢሮክራሲ ሳይኖርበት ሠርቶ ሀገሩንና ራሱን ተጠቃሚ የሚያደርግበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠርም ገልፀዋል።
በከተማ አስተዳደሩ በጣም አዋጭ በሆኑ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ እንዲሠማሩም ጠይቀዋል።
የባሕር ዳር ከተማን የትምህርት እና የቱሪዝም ከተማ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከተማዋ በርካታ ጎብኚዎች የሚጎበኟት ከተማ መሆኗንም አንስተዋል። ታላላቅ ሆቴሎችን በመገንባት የቱሪዝም መዳረሻ እንዲያደርጓትም ጠይቀዋል።
ከተማዋን ለኮንፍረስ ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ በመሆኑ በሆቴል ቱሪዝም የሚሠማሩ ባለሀብቶች ትርፋማ እንደሚሆኑ ነው የተናገሩት። በሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮችም በከተማዋ መሥራት የሚያስችል እድል እንዳለ ነው የተናገሩት።
የዳያስፖራ አባላት መሥራት በሚፈልጉት መስክ ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ ቢያቀርቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት እንደሚቻልም አስታውቀዋል። ተዘጋጅቶ ለሚመጣ ሁሉ በአፋጣኝ ምላሽ ይሰጠዋልም ብለዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት መሠማራት የሚፈልግ ካለም የፕሮጀክት ዕቅዶችን በማስገባት በአፋጣኝ ሥራ መጀመር እንደሚቻልም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በመሥራት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል። የሚያለያዩ ነገሮችን በመጠየፍ አንድ በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ በማተኮር ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሀገር ለመገንባት የዳያስፖራው ሚና ከፍ ያለ መሆኑንም አንስተዋል።
ከፖለቲካው ምስቅልቅል በመውጣት አፍሪካን የምታስተሳስር ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት መሥራት ይገባልም ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው በመነሳታቸው የጠላትን ሀገር የማፈራረስ ዓላማ መና አስቀርተውታልም ነው ያሉት።
ከተገኘው የአንድነት ልምድ በመነሳት የበለጠ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመድረኩ የተገኙ የዳያስፖራ አባላት ስለ ሀገር ሞተው ሀገርና ሕዝብን ያኮሩ ጀግኖች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በመሥራት ሀገርን ማሳደግ እንደሚገባ መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
+3
0
People reached
0
Engagements
Boost post
Like
Comment
Share
Exit mobile version