Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጥምቀት በዓልን በጎንደር በድምቀት ለማክበር ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥምቀትን በዓልን በጎንደር ከተማ ”የአንድነት ደወል ጥምቀትን በጎንደር” በሚል መሪ ቃል ለማክበር ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ ተናገሩ።

ምክትል ከንቲባው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ከጥር 5 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ ለሚከበረው የጥምቀት በዓል አካል ለሆነው የባህል ሳምንት የተለያዩ ዝግጅቶች ይደረጋሉ፡፡

በዚህም መሰረት የፊታችን ጥር 8 ቀን ለአሸናፊዎች ሮጣለሁ! በሚል መሪ ቃል የፋሲል ከነማን ገቢ ለማሳደግ ያለመ የሩጫ ውድድር ይካሄዳል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በከተማዋ በሳምንቱ ግጥምን በማሲንቆ የተሰኘ መርሃ ግብር እንደሚካሄድ ነው የገለጹት፡፡

ጥር 9 ቀን ደግሞ በህልውና ዘመቻው ለተሳተፉ አካላት የምስጋና መርሃ ግብር የንጉስ ራት የተሰኘ ፕሮግራም እና መሰል መርሃ ግብሮች ይከናወናሉ ነው ያሉት።

ለበዓሉ አከባበርም ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።

በዚህም ከመከላከያ፣ ከአድማ ብተና፣ ከፌደራል ፖሊስ እና ከግል ታጣቂዎች ጋር የጸጥታ መዋቅሩ ተጠናክሮ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በከተማዋ ተጥሎ የነበረው የሰዓት ገደብ አሁን ላይ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ተጣርቶ ገደቡ መነሳቱን ምክትል ከንቲባው አስታውሰዋል።

በለይኩን ዓለም

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version