Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አፍሪካውያን እኛ እናውቅላችኋላን ከሚሉ ወገኖች ተፅእኖ ነፃ ለመውጣት በአንድ መቆም ይጠበቅባቸዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካውያን እኛ እናውቅላችኋላን ከሚሉ ወገኖች ተፅእኖ ነፃ ለመውጣት በአንድ መቆም ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ምሁራን ተናገሩ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካ እና የኤዥያ ጥናት መምህር ዶክተር ጌታቸው ካሳ፥ ከ400 አመት በላይ አሜሪካንን በመገንባት ታሪክ ውስጥ ጥቁሮች ያበረከቱት ሚና ቀላል አልነበረም ይላሉ ።

ነገር ግን በዚያ ሁሉ ጊዜ ጥቁሮች ያበረከቱት ነገር ፋይዳ እንደሌለው በማሰብ እንደሰው ሳይቆጠሩ በብዙ ጭቆና ውስጥ በመኖራቸው ይህ ይበቃል ያሉ ጥቁሮች እጣ ፈንታቸው ሞት ነበር ነው ያሉት፡፡

በአፍሪካ በተለያየ ዘመነ መንግስት የነበሩ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ስለፓን አፍሪካኒዝም ሲያቀነቅኑ የነበሩ ቅኝ ግዛትን በመቃወም ከቅኝ ግዛት በኋላም ምእራባውያን በእጅ አዙር አፍሪካን በእጃቸው መዳፍ ውስጥ ለማቆየት እየተደረገ የነበረ እንቅስቃሴን የተቃወሙ፣ ኤምፔርያሊዝምን ተፃርረው የቆሙም በርካታ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ፀሀፊ እና ጋዜጠኛ አቶ ሰለሞን ዳኜ በበኩላቸው፥ “አፍሪካ ማደጓ ለምዕራባውያን የሚፈጥረው ራስ ምታት ትልቅ ነው፤ ለዚያም ነው የአፍሪካ በብዙ መንገድ ሰላም ማጣት ለእነሱ ድሎት በመሆን እስካሁን የቀጠለው” ይላሉ ፡፡

በቅኝ ግዛት ያልተገዛችው ኢትዮጵያ፥ ፓን አፍሪካኒዝምን የሚያቀነቅኑ በተለያዩ ጊዚያት የተነሱ ህዝብም መንግስትም ነበራት ነው ያሉት፡፡

ዛሬም የአፍሪካን መበልፀግና በራስ መቆም አልፎ በአንድ መሰለፍን የሚያስቡ መንግስታት ሆነ ግለሰብ የሚደርስባቸው ተፅእኖ ቀላል አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።

ዛሬም አፍሪካ ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶች አልፎም በድህነት የመኖር ሚስጥር እናውቅላቹሀለን ብለው የሚነሱ ሀገራት የሚፈጥሩት በመሆኑ አፍሪካውያን ይህ ገብቷቸው በአንድ መቆም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በቅድስት ተስፋዬ

Exit mobile version