Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የ100 ሚሊየን ብር የአይነት ድጋፍ አደረገ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሶማሌ ክልል በድርቅ ምክንያት ለተጎዱ ወደ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን የሚገመቱ ወገኖች የሚሆን የ100 ሚሊየን ብር ዋጋ ያለው የምግብ ቁሳቁስ እና የእለት ደራሽ ድጋፍ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ አስረክበዋል፡፡

በድጋፍ ርክክቡ ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፥ ‘‘ህመማችሁ ህመማችን ነው ፤ችግራችሁ ችግራችን ነው፤ እናንተ ላይ የደረሰው ጉዳት ሁላችንም ላይ የደረሰ ነው ይሰማናል’’ ብለዋል፡፡

‘’ሃገራችን አሁን የገጠሟትን ችግሮች መሻገር የቻለችው አብረን በመቆማችን ነው ያሉ ሲሆን ፥ አሁንም አብረን ከሆንን አሁን የገጠመን ችግር እጅግ ቀላል ነው፤ እናልፈዋለን፤ ይህንን የማድረግ ጉልበትም አቅምም እሴትም ልምድም አለን’’ ብለዋል፡፡

ድጋፉ የመጀመርያ ዙር መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ ፥ በዚህኛው ዙር ለምግብ ቁሳቁሶች ቅድሚያ የሰጠነው ቅድሚያ ለሰው መስጠት ስለሚያስፈልግ ነው ብለዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሶማሌ ክልል የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም ሃገራዊ ግዴታውን ለመወጣት የበኩሉን እያደረገ ነው ያሉ ሲሆን ፥ ከተማ አስተዳደሩ ለሰጠው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

በክልሉም ድርቁ ወደ ርሃብ እንዳይቀየር ሰፊ ርብርብ እየተካሄደ መሆኑንና መንግስት የአጭርና የረጅም ጊዜ ስራዎችን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ማንሳታቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ  ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ድጋፉን ለመስጠት ዛሬ ነበር ጅግጅጃ ከተማ የገቡት።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version