አዲስ አበባ፣ታህሳስ 6፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር በአማራ ክልል በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ለተጎዱ ወገኖች የሚውል 150 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉን ያስረከቡት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ፤ ጠላቶቻችን ባሰቡልን ሳይሆን በድል ስለተገናኘን እንኳን ደስ ያለን ብለዋል። የሽብር ቡድኑ የገጠመው ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ነው ያሉት ሚኒስትሯ የሽብር ቡድኑ ከዓመታት በፊት ጦርነት እንደጀመረም አስታውሰዋል።
የሽብር ቡድኑን በአንድነት ማሸነፍ መቻሉንም ገልፀዋል። ድሉ የመጨረሻ አለመሆኑንም በማመላከት።
ጠላቶቻችን አንገት እንድንደፋ ፈልገዋል እኛ ይሄን አንፈቅድም ፣ እኛ ጦርነቱን እንደ እድል ተጠቅመን ብርሃኑን ብቻ እያየን መጓዝ አለብን ነው ያሉት። የወደሙ ከተሞቻችን የውስጥ ኃይልን በመጠቀም እና ከተሞችን በማስተሳሰር የበለጠ አድርጎ መገንባት ይገባል ብለዋል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርም ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን በአማራ ክልል ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል። የተጎዱ ከተሞችን ሌሎች ከተሞች እንዲደግፏቸው ከተሞችን እያስተሳሰሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የአማራ ክልል ለዘመናት ያካበተው ሀብት በመዘረፉና በደል ስለደረሰበት ሕዝቡ ልቡ ተነክቷል ያሉ ሲሆን የወራሪው ቡድን ዋና ዓላማ ኢትዮጵያን ማደህየት፣ ማፍረስና ኢትዮጵያውያንን ማለያየት እንደሆነም ገልፀዋል።
ጦርነቱ አሁንም አልተቋጨም ጥቃቱ የመላው ኢትዮጵያውያን በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በጋራ ተነስተው ጠላት ደምስሰዋል መደምሰሰ አለባቸዉ ብለዋል፡፡
ከነበረው የተሻለ አድርጎ ለመገንባት የሚያስችል እድል ያመጣ፣ የአማራ ክልል ሕዝብ ደራሽ ወገን እንዳለው ያረጋገጠበት እድል ነዉ ያሉት ረዕሰ መስተዳደሩ መላ ኢትዮጵያውያን ከጎናችን እንደሆኑ አረጋግጠናል ማለታቸዉን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

