Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አገልግሎቱ በአማራና አፋር የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉባቸውን ችግሮች ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ እንደሚሰራ ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በአማራና አፋር ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉባቸውን ችግሮች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ እንደሚሰራ አስታወቀ።

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ሰራተኞች በላሊበላ ከተማ በአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ሀይል ውድመት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የህክምና ቁሳቁሶችን በድጋፍ አበርክተዋል።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ፥ በላሊበላ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ርክክብ ሥነ-ስርዓት ላይ እንዳሉት፥ የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች ለህልውና ዘመቻው ስኬታማነት ከ13 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

በአሁኑ ወቅትም በአሸባሪው የህወሓት ወራሪ ሀይል በአማራና አፋር ክልሎች ውድመት ለደረሰባቸው ተቋማትና ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ከተቋሙ ሰራተኞችና ከአጋር አካላት 28 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ምግብና ቁሳቁስ መሰብሰቡን ገልፀዋል።

ከተሰበሰበው ውስጥ በላሊበላና ሰቆጣ ከተሞች ዘረፋና ውድመት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማትን አገልግሎት ለማስጀመር የሚያግዙ የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለከተሞቹ የጤና ተቋማት 18 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ፍራሾች፣ ብርድ ልብስ፣ የተለያዩ መድሃኒቶች እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለፃ ፥ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ የደረሱ ጉዳቶችን ለማቃለል ከሚያደርገው ድጋፍ ጎን ለጎን የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉባቸውን ችግሮች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ለማድረግ ይሰራል።

በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና ንብረታቸው የወደመባቸውን ዜጎች ወደ ቀደመ ህይወታቸው እንዲመለሱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሊረባረቡ እንደሚገባም ነው አቶ ተስፋሁን ያሳሰቡት።

የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ማንደፍሮ ታደሰ በበኩላቸው እንዳሉት ፥ የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈፀመበት ወቅት በከተማዋ በግልና በመንግስት ንብረት ላይ ውድመት ፈፅሟል።

በተለይም የአሸባሪው ወራሪ ሀይል በላሊበላ ሆስፒታልና ጤና ጣቢያ ላይ ዘረፋ በመፈፀሙ ምክንያት ዜጎች ለከፋ ማህበራዊ ችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል።

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ሰራተኞችና አጋር አካላት ያደረጉት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ በከተማው ጤና ተቋማት የግብዓት እጥረትን የሚያቃልል መሆኑንም ያመላከቱት።

ምክትል ከንቲባው አገልግሎቱ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፥ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውንም ነው ኢዜአ የዘገበው።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version