አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት በሰብዓዊ መብት ስም ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት የውስጥ ጉዳይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ኢራን በጽኑ እንደምትቃወም በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር ሰመድ አሊ ላኪዛዴህ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ሰብዓዊ እሴቶች ለሁላችንም ዋጋ ያላቸው ሃብቶች በመሆናቸው የምዕራባውያንን ጣልቃ የመግባት ፍላጎት ለማሟላትና ለኒኦ-ኮሎኒያሊዝም ማስፈጸሚያ ሲባል መሸርሸር የለባቸውም ብለዋል፡፡
በዚህም ምዕራባውያን ሀገራት ሰብዓዊነት የሚሉትን ተረክ በማንሳት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና ህገ -ወጥና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢራን ይህንን ድርጊት እንደምትቃወም ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ጠንካራ፣ ነጻና ሉዓላዊነቷ የተከበረ ኢትዮጵያን ማየት ስለማይፈልጉ ሰብዓዊ እሴቶችን በመጥቀስ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት በቅኝ አገዛዝ ስር ያልወደቀች ብቸኛ ሀገር መሆኗን አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ ነጻነት በመላው ዓለም የጸረ-ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄን በማነሳሳት ይታወቃል ብለዋል።
የምዕራባውያን ሀገራት ላለፉት 42 ዓመታት በኢራን ላይ ሁሉንም አይነት ጫና ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው ፥ ከዚህ አኳያ “ሰብዓዊ መብት” በማለት በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለውን ጣልቃ ገብነት ኢራን ትገነዘባለች ነው ያሉት፡፡
የምዕራባውያን ጣልቃገብነት ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ አፍጋኒስታንና ሌሎች መሰል ሀገራትን ለከፋ ቀውስ መዳረጉንም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ የምዕራባውያኑን ጫናና ጣልቃ ገብነት በመቃወም የምታደርገው ትግል በርካታ አፍሪካውያን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን እንዲታገሉ እንደሚያነሳሳ አብራርተዋል፡፡
ኢራን የምዕራባውያኑን ጫናና ማዕቀብ የተቋቋመችበትን ልምድ ለኢትዮጵያና ሌሎች ወዳጅ ሀገራት ለማካፈል ፈቃደኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል፡፡
ሀገራቸው ጫናዎችን ተቋቁማ በሳይንስ፣ መከላከያ፣ ሳይበር ደህንነት፣ ናኖ ቴክኖለጂ፣ ባዮ ቴክኖሎጂ፣ ሳተላይትና ግብርና ከፍተኛ እድገት ማስመዝገቧንም ነው አምባሳደሩ ያብራሩት።
ኢትዮጵያና ኢራን ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው ፥ ኢራን የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደምትሻ ተናግረዋል፡፡
ኢራን በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን ከከፈተች 71 ዓመታት ተቆጥሯል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

