አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከባድ የሰው መግደል ወንጀል የፈጸሙ ተከሳሾች በሞት እና በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው።
ቅጣቱ የተላለፈው በ1ኛ ተከሳሽ ሃብታሙ /ጊታር/ እንዳላማው፣ 2ኛ ተከሳሽ ምስጋናው /ጉቸ/ ደርሶ ፣3ኛ ተከሳሽ ሃብቱ /ማስተር/ ሲሳይ በተባሉ ተከሳሾች ላይ ነው።
ቅጣቱ ሊወሰን የቻለው ተከሳሾች ሆን ብለው ሰውን ለመግደል በማሰብ ጥር 16 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 9 ስዓት በሚሆንበት ጊዜ፥ በባህርዳር ከተማ ቀበሌ 17 ልዩ ቦታው ከቀድሞው ከብት ገበያ ሰርክሉ አካባቢ ላይ ሟች ታዘበው ንጋቱ የተባለውን ግለሰብ 1ኛ ተከሳሽ ድንጋይ ወርውሮ ጭንቅላቱን በመምታት እንዲወድቅ ካደረገ በኋላ፥ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች የሟችን ሆድ፣ቀኝ ክንዱንና ጀርባውን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ደጋግመው በጩቤ በመውጋት ህይወቱ እንዲያልፍ አድርገዋል።
በመሆኑም ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ዐቃቢ ህግ የሰውና የጽሁፍ ማስረጃዎችን ዘርዝሮ ክስ በማቅረቡ መሆኑ ተመላክቷል።
ተከሳሾች በችሎት ቀርበው ድርጊቱ ተፈጽሟል፤ አፈጻጸሙ ግን እራሳችንን ለማዳን የተፈጸመ ህጋዊ መከላከል እንጂ ሆን ብለን ለመግደል በማሰብ የተፈጸመ አይደለም በማለት ተከራክረዋል።
ዐቃቢ ህግ በበኩሉ፥ ተከሳሾች መብታቸውን ጠብቀው የተከራከሩ ስለሆነ ሆን ብለው ወንጀሉን የፈጸሙት ስለመሆናቸው የሚያስረዱ ማስረጃዎች ቀርበው እንዲሰሙ በማለቱ ማስረጃዎችን አስቀርቦ አሰምቷል።
የዐቃቤ ህግ ማስረጃዎችም ተከሳሾች የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት አስበው መሆኑን በዝርዝር አስረድተው ያረጋገጡባቸው ስለሆነ፥ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ፍ/ቤቱ ብይን ቢሰጥም የዐቃቤ ህግን ማስረጃዎች ማስተባበል ባለመቻላቸው የወንጀል ህግ አንቀጽ 539 ንኡስ አንቀጽ 1 “ሀ” ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ ተላልፈው ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ፈጽመው በመገኘታቸው ጥፋተኛ ተብለዋል።
ፍርድ ቤቱም የተከሳሾችን ጥፋተኝነት ተከትሎ በዐቃቢ ህግና በተከሳሾች በኩል የቀረበውን የቅጣት አስተያየት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆንቸው በማቅለያነት በመያዝ፣ 3ኛ ተከሳሽ የቅጣት ማቅለያ ምክንያት የሌለው መሆኑን ከተገቢው ህግ ጋር ከመረመረ በኋላ ተከሳሾችን ያርማል፣ ያስተምራል፣ ሌሎችንም ያስጠነቅቃል ብሎ ያመነበትን 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ፣ 3ኛ ተከሳሽ በሞት ቅጣት እንዲቀጣ የባህርዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት ውሳኔ ማስተላለፉን ከአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

0
People reached
0
Engagements
–
Distribution score
Boost post
Like
Comment
Share