Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በዓላት ሠላምና አብሮ የመኖር ዕሴትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲከናወኑ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሁሉም በዓላት ሠላምና አብሮ የመኖር ዕሴቶችን በሚያጠናክር መልኩ እንዲከናወኑ ጥሪ አቀረበ፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በዓላት እና ማንኛውም ሃይማኖታዊ ወይም ማኅበራዊ ስብስቦች የማኅበረሰባችንን የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር ዕሴቱን በሚያጠናክር መልኩ እንዲከወኑ ነው የጠየቀው፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ የዳበረ የመከባበርና በሠላም አብሮ የመኖር ዕሴት ያላት መሆኑን ያወሳው መግለጫው፥ ዜጎቿ ሃይማኖታዊ ማንነታቸው ሳይለያያቸው ክፍለ ዘመናትን የተሻገሩ ስለመሆናቸው የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱ ገልጿል፡፡

ከሁሉም በላይ ሃይማኖቶች የሰላም፣ የመከባበር፣ የመረዳዳት፣ የፍቅር እና የትብብር መሰረቶች በመሆናቸው ምዕመናን ይህንን በተግባር ሲገልጡ ኑረዋል፤ እየኖሩም ይገኛሉ ብሏል ጉባኤው በመግለጫው፡፡

በአንፃሩ ጥል፣ ፀብ ጫሪነት እና አዋኪነት ሁሉ በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ የተወገዙ መሆናቸውንም አስረድቷል፡፡

አንዳንድ ግለሰቦች በሃይማኖት ሽፋን የሚያደርጉት ህገ ወጥ የጥላቻ ንግግር፥ ከየትኛውም የሃይማኖት አስተምህሮ ጋር የሚቃረን እና በመከባበርና በሠላም አብሮ የሚኖረው አማኝ ሠላማዊ መስተጋብሩን የሚያጠናክር ባለመሆኑ ከዚህ መሰሉ ተግባራቸው እንዲታቀቡም አሳስቧል፡፡

ማንኛውም ሃይማኖታዊም ሆነ ማህበራዊ በዓላት የሁሉንም ኢትዮጵያውያን አብሮነት እና ኢትዮጵያዊ አንድነታቸውን በማጠናከር እንዲከበሩ ጉባኤው ጥሪ ማቅረቡን ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፤ እንገንባ፤ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version