Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በጅግጅጋ ከተማ ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች እየተካሄዱ ነው – የዳያስፖራ አባላት

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 9፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅግጅጋ ከተማ ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች እየተካሄዱ መሆኑን መመልከታቸውን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ የሶማሌ ክልል ተወላጅ ዳያስፖራዎች ገለፁ።
የሶማሌ ክልል ተወላጅ የዳያስፖራ አባላት ከክልሉ የኢንቨስትመንትና ዳያስፖራ ቢሮ እና ከጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ጋር በከተማው ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት የበቁትን የጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ ፤ የሚሽን ፥ የአየር ደጋና የዱአሌ የአስፋልት መንገዶችን እንዲሁም ሌሎች የአስፋልት የመንገድ ግንባታዎችን ተመልክተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀሺ በሰጡት ማብራሪያ÷ ባለፉት ሶስት ዓመታት በጅግጅጋ ከተማ 11 የአስፋልት መንገዶችን ለማስገንባት በተያዘው እቅድ መሠረት አብዛኞቹ የአስፋልት መንገዶች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠታቸውን ጠቁመው፥ ቀሪዎቹም በግንባታ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከተማውን አረንጓዴና ለመኖሪያ ተስማሚ ውብ ከተማ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ከንቲባው፥ የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራዎች በከተማው እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶችን በመመልከታቸው ምስጋና አቅርበዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ የክልሉ ተወላጅ ዳያስፖራዎች በጉብኝቱ÷ በጅግጅጋ ከተማ ተስፋ ሰጪ የልማት ስራዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውንና ከለውጡ ወዲህ በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ልማት መረጋገጡን መታዘባቸውን ገልፀዋል።
የጅግጅጋ ከተማንና የክልሉን ልማት ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ መናገራቸውን ከሶማሌ ክልል ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፤ እንገንባ፤ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version