Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጥምቀት በዓል ድንቅ የኢትዮጵያዊነት ማሳያ ፣ ድምቀታችንና የሀገራዊ ኩራታችን ምንጭ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥምቀት በዓል በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት ከተመዘገቡ ድንቅ የኢትዮጵያዊነት ማሳያ፣ውድ ሀብታችን ፣ ድምቀታችንና የሀገራዊ ኩራታችን ምንጭ ከሆኑ በዓሎቻችን አንዱ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች  እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሠላም አደረሳችሁ አደረሰን ሲሉ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከንቲባዋ ÷ ጥምቀት የፍቅር ፣ የሠላም ፣ የደስታ ፣የአብሮነት፣ የመተሳሰብ ፣የፀሎት እና የበጎነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በጥምቀት በዓል ጥላቻ በጥምቀተ- ባህሩ በፍቅር ታጥቦ የሚነፃበት ፣ መለያየት በአንድነትና ፍቅር  የሚተካበት ፣ ቂም ለይቅርታ እና አብሮነት ቦታውን የሚለቅበት፣ ፀብ በእርቀ ሰላም የሚዘጋበት ፣ አንደበቶች ፍቅርን የሚዘሩበት ፣ የጥላቻ መሰረቶች የሚናዱበትና ሠላምና ደስታ የሚነግስበት  ወቅት ነው ብለዋል፡፡

በተለይም የዘንድሮ የጥምቀት በዓል በሀገራችን ሉዓለዊነት ላይ የተቃጣውን ወረራና ጦርነት በአንድነትና በከፍተኛ ኢትዮጵያዊ ወኔ በመከትንበት ማግስት የምናከብረው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አሁንም ይህንን ህብረታችንንና አንድነታችነን አጠናክረን የምንቀጥልበት፤ ለልዩነቶች በር የሚከፍቱ እድሎችን የምንዘጋበት፤ የኢትዮጵያን ትንሳኤ በአንድነታችን ላይ የምናፀናበት በዓል ይሁንልንም ነው ያሉት፡፡

ጥምቀት ለከተማችን አዲስ አበባ ልዩ ገፅታን የሚያላብስ የዓይን ማረፊያ በዓሎቻችን አንዱ በመሆኑ  በዓሉ በድምቀት እንዲከበር፣ በሠላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ   አስተዋዩ ፣ ጨዋውና ሰላም ወዳዱ  የከተማችን ህዝብ ወትሮም እንደምናደርገው ሁሉ  በትብብርና በአብሮነት አካባቢያችንን  በንቃት በመጠበቅ፣ ከፀጥታ ሃይሎቻችን ጋር በትብብር በመስራት እናሳልፈው ዘንድ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፤ እንገንባ፤ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

Exit mobile version