አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው የህወሃት ዝርፊያና ውድመት የደረሰበት የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተደረገው ርብርብ ወደ ስራ መመለሱን የፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ሰኢድ ገልፀዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ ÷ ሁሉም የሚመለከተው የመንግስት እና የህብረተሰብ አካል በእልህ እና በቁጭት በመስራት ለስራ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ተሟልተውና መሰረተ ልማቶች ተጠግነው ፓርኩ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡
በፓርኩ ውስጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለማሳለጥም በአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ስር የሚገኙ እንደ ባንክ፣ ጉምሩክ እና ሌሎችም ሴክተሮች ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
ፓርኩ የደረሰበትን ከፍተኛ ጉዳት በማስተካከል በአጭር ጊዜ ወደስራ እንዲመለስ በማድረጉ ሂደት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች፣ የፓርኩ ጠንካራ ሰራተኞች፣ የባለሃብቶች ቁርጠኝነት፣ የተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ድጋፍ ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ እና የጸጥታ ሃይሎች ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
አሁን ላይ ወደስራ የገቡ የአምራች ድርጅት ሰራተኞች ወደ ማምረት ሂደት በአፋጣኝ የገቡ ሲሆን ÷ሌሎች በሂደት ላይ የሚገኙ አምራች ድርጅቶችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ በመግባት በቅርቡ ኤክስፖርት ለመጀመር እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሰረተ ልማቶች የተሟሉለት እና አለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባ መሆኑ ተገልፆ÷ አሁን ላይ በፓርኩ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ የሀገር ውስጥም ይሁን የውጪ ሀገር ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎች እንደተመቻቹ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፤ እንገንባ፤ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

