አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 43ኛው የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ መልዕክተኞች ስብስባ ዛሬ ተጀምሯል።
ስብሰባው “የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ማፋጠን” በሚል የአፍሪካ ሕብረት ባዘጋጀው የ2022 መሪ ቃል እየተካሄደ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በበይነ መረብ እየተካሄደ ባለው በዚህ ስብሰባ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማህማት እና የሕብረቱ አባል አገራት አምባሳደሮች እየተሳተፉ እንደሆነ ኢዜአ ዘግቧል።
ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆየው ስብሰባ ጥር 25 እና 26 ቀን 2014 ዓ.ም ለሚካሄደው 40ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ እንዲሁም ጥር 28 እና 29 ቀን 2014 ዓ.ም ለሚከናወነው 35ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ ረቂቅ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም ኮሚቴው በአፍሪካ ሕብረት ስር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት የአፈጻጸም እንዲሁም ሕብረቱ እ.አ.አ በ2021 ያካሄዳቸውን ስብስባዎች የተመለከቱ ሪፖርቶችን ያደምጣል።
40ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤትና 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

