አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተራ እና የጥምቀት በዓል በመላው አማራ ክልል ሀይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም መጠናቀቁን የአማራ ክልል መንግስት ገልጿል።
በከተራ እና በጥምቀት አከባበር ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የክልሉ የመንግስት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙልነህ÷ የከተራ እና የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በሁሉም የአማራ ክልል አካባቢዎች በሰላም ተጠናቋል ብለዋል።
በዓላቱ በሰላም መጠናቀቃቸው የአማራ ክልል ሀገራዊ እና አለም አቀፋዊ ሁነቶችን በሰላም ማስተናገድ የሚችል መሆኑን ያመላክታል ነው ያሉት።
በዓሉ ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ታዳሚዎች እና ዳያስፖራዎች በተገኙበት ጠላቶቻችን በተመኙት ሳይሆን በህዝባችን ትብብር እና ቁርጠኝነት በመላው የክልሉ አካባቢዎች በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል ብለዋል።
በጎንደር የታየው የጥምቀት በዓል አከባበር ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ ድምቀት መከናወኑን ነው አቶ ግዛቸው የተናገሩት።
የአማራ ህዝብ በዓላቱ በሰላም እንዲጠናቀቁ ላደረገው ከፍ ያለ ተሳትፎ ምስጋና የሚገባው እንደሆነም በመግለጫው አንስተዋል።
የበዓላቱ በሰላም መከበር ጠላቶቻችንን ተስፋ ያስቆረጠ፥ ለህዝባችን ደግሞ ተስፋን ያላበሰ ነው ብለዋል ።
አያይዘውም ክልሉ ይህንን አኩሪና ታላቅ ሁነት ለዓለም ማሳየቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ለማነቃቃት ይረዳልም ነው ያሉት።
በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ የላቀ ተሳትፎ ላደረጉ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና የፀጥታ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
በነገው ዕለት በአባይ መነሻ የጊዎን በዓል፣ በጥር 23 ደግሞ የአገው ፈረሰኛች የሚያከበሩት በዓላትም በሰላም እንዲጠናቀቁ በጋራ እንሰራለን ብለዋል አቶ ግዛቸው በመግለጫቸው።
በክብረወሰን ኑሩ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

