Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ማለፉን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በዓለም ደምቃ እንድትታይ ከሚያደርጓት በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ማለፉን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ በበዓለ ጥምቀቱ የታዩት ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ዕሴቶች በዓሉ የኢትዮጵያውያን ለዘመናት የዘለቀ ውብ አብሮነትንም ለዓለም ያሳየ ነው ብሏል።

በዓሉ በመላ ሀገሪቱ በሰላም እንዲከበር ኅብረተሰቡና የጸጥታ አካላት ላደረጉት አስተዋጽዖ መንግሥት ከፍተኛ ምስጋናውን ያቀረበው መግለጫው፥ በዓሉ የኢትዮጵያውያንን መፋቀር፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ሰላም በሚገልጽ መንገድ እንዳይከበር የተለያዩ አካላት የሸረቧቸውን ሤራዎች ሕዝቡና የጸጥታ አካላት ተናብበውና ተቀናጅተው ማክሸፋቸውን ነው ያመለከተው።

ኢትዮጵያ የምታስተናግዳቸው ታላላቅ ዓለም አቀፋዊ ክንውኖች ከፊታችን አሉ ያለው መግለጫው፥ እነዚህ ክንውኖች እንዳይሳኩ የኢትዮጵያን ገጽታ ማበላሸት የፈለጉ አካላት የጥምቀትን በዓል በመረበሽ ተልኳቸውን ለማሳካት ሞክረው ነበር፤ ነገር ግን አልተሳካላቸውም ብሏል።

የሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው የመጡት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የማኅበራዊ መስተጋብሩ አካል በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች ተገኝተው በዓሉን ማድመቃቸውን አመልክቷል።

የጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊ በዓልነቱ ባሻገር ለኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ ግንኙነት፣ ለቱሪዝም መስሕብነትና ኢትዮጵያን ለዓለም በማሳየት ታላቅ ሚና አለው ያለው መግለጫው፥ በዚህም የተነሣ ከበዓሉ ቀደም ብሎ በተደረገ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት የሃይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው መስተዳድር አመራሮች፣ የጸጥታ አካላትና ወጣቶች በጋራ በመሥራት በዓሉ በአብዛኛው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ መቻሉን ጠቅሷል።

የጥምቀት በዓል በመላ ኢትዮጵያ በደመቀና በሰላማዊ መንገድ ቢከበርም በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ እና በቡራዩ አዋሳኝ ወይ ብላ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ በተፈጠረው ችግር ግን በዓሉ መስተጓጎሉና በሰዎች ላይም ሞትና ከባድ ጉዳት መድረሱ አስታውቋል።
በዓሉ በተገቢው መንገድ ባለመከበሩ፣ እንዲሁም በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ኀዘን ይገልፃል ያለው መግለጫው፥ መንግሥት በስፍራው የተፈጠረውን ክሥተት በማጣራት ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለሕግ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

ለዘመናት የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫ እንዲሁም የጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብራችን ማሳያ በሆኑ እንደ ጥምቀት በዓል ያሉ ሀብቶቻችንን ለማደብዘዝ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር እንደሚከሽፍም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version