አዲስ አበባ ፣ጥር 16 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ።
በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሕዝባዊ ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው፡፡
በህዝባዊ ኮንፍረንሱ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል÷ የመልሶ ግንባታ ስራው በፍጥነት እንዲከናወን በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንን ተግባር ለማገዝም ከክልሎች፣ ከዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እና ከባለሀብቶች ጋር እንዲሁም ባንኮችም ብድር እንዲያመቻቹ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
የትምህርትና የጤና ተቋማትን እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ ተቋማትን መልሶ የመገንባትና ወደ ስራ የመመለስ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የመልሶ ማልማት ስራውን ለማሳለጥ ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ርእሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል ።
የወሎ ኦሮሞ ህዝብ ክብሩንና ኢትዮጵያዊነቱን ዳግም ያሳየ መሆኑንም ዶክተር ይልቃል ገልጸዋል፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ህዝብ አሸባሪዎቹን ሸኔንና የህወሃትን ወራሪ ቡድን ለመደምሰስ በተደረገው ተጋድሎ ትልቅ ድርሻ ነበረው ያሉት ዶክተር ይልቃል ÷የዞኑ ህዝብ በደጀንነትና በጦርነቱ በቀጥታ በመሳተፍ አኩሪ ታሪክ ጽፏል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በግንባር ያስመዘገብነውን ይህንን አኩሪ ተግባር፥ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅና የልማት ተግባራትን በማከናወን ልንደግመው ይገባል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በሙሉቀን አበበ

