አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ከተማ በመገኘት በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አካላት ከ9 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።
“በጀግንነት እንጠብቃለን ህዝባዊ ወገንተኝነታችንን በድጋፋችን እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል የተደረገው ድጋፍ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አካላት እና ለወደሙ የፖሊስ ተቋማት ማቋቋሚያ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ በጥሬ ገንዘብ 1ሚሊየን ብር ፣ ከ 1ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ልዩ ልዩ አልባሳት ፣ ከ1ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የፅዳት እቃዎች ፤ 762 ሺህ ብር የሚያወጡ የምግብ ፍጆታዎች ፣ ከ51 ሺህ ብር በላይ የሚሆኑ ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን እና ከ4 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የቢሮ እቃዎችን በአጠቃላይ ከ 9 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ተብራርቷል።
የአማራ ክልል ፖሊስ የሰው ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ ረ/ኮሚሽነር ሀብታሙ ሲሳይ፥ ክልሉን ከአሸባሪው የትሕነግ ቡድን ነፃ ከማድረግ ባሻገር ከልዩ ልዩ ሀገር ወዳድ ግለሰቦችና ተቋማት ጋር በመሆን የወደሙ ሀብቶችን የማደራጀት ሥራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በተለያዩ ዘርፎች ክልሉን መልሶ ለማደራጀት የሚደረጉ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያሳወቁት ኃላፊው፥ የአዲስ አበባ ፖሊስ ላሳየው ወገኝተኝነት እና ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በሽብርተኛው ህወሃት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባትን እና ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ለማቋቋም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!