አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በቀወት ወረዳ በመስኖ ክላስተር የተዘራ የስንዴ ልማትን ጎበኘ፡፡
በጉብኝት መርሀ ግብሩ የክልል ከፍተኛ አመራሮች አና የሰሜን ሸዋ ዞን የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ÷ የክልሉ ህዝብ በዘንድሮው ዓመት ከአሸባሪው ህወሓት ጥቃት ቢፈፀምበትም ወራሪውን ቡድን ለመዋጋት ካደረገው ተጋድሎ ጎን ለጎን የልማት ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አድንቀዋል፡፡
አርሶ አደሩ ያስመዘገበው ምርታማነት በቀጣይም በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ ሊደገም ይገባል ነው ያሉት።
የአካባቢው አርሶ አደሮች በበኩላቸው ÷ የቆላ መስኖ ስንዴ ያለሙት ከአሸባሪው ህወሓትን በመፋለም በአንድ እጃቸው የጦር መሳሪያ፥ በሌላኛው የግብርና መሳሪያቸውን በመያዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የቆላ ስንዴ በአካባቢው በብዛት አለመተግበሩን ጠቅሰው÷ በቀጣይ በሰፊው እንደሚያለሙ ተናግረዋል ።
ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከሚሴ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ሕዝባዊ ኮንፍረንስ ላይ ተገኝተው በግንባር ያስመዘገብነውን አኩሪ ድል፥ የልማት ተግባራትን በማከናወን ልንደግመው ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።
በኤልያስ ሹምዬ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

