Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት በጥሩ ሂደት ላይ መሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ህብረት 35ኛው የመሪዎች ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ብሄራዊ ኮሚቴው ገለጸ፡፡
 
የአፍሪካ ህብረት 35ኛው የመሪዎች ጉባኤና 40ኛው የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባን ለማስተናገድ የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶችን አስመልክቶ ብሄራዊ ኮሚቴው ግምገማ አካሂዷል።
 
በወቅቱም ከ20 በላይ የብሄራዊ ኮሚቴው አባል ተቋማት ለጉባኤው እያደረጉ ያሉትን ቅድመ ዝግጅት አቅርበው ውይይት የተደረገ ሲሆን÷ ቅድመ ዝግጅቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለ ተገልጿል።
 
እንግዶች ከአየር ማረፍያ እስከ ሆቴሎችና የስብሰባ አዳራሽ ደህንነታቸው ተጠብቆ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ተግባራዊ ዝግጅቶች በመልካም ሁኔታ ላይ እንዳሉ ተጠቁሟል።
 
መሰረተ ልማቶችን መልሶ ከመጠገንና ያለምንም እንከን አስተማማኝ አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረግ አንፃር ጥሩ ስራዎች በተቋማዊ ቅንጅት እየተሰሩ መሆኑም ተገልጿል።
 
ከጤና አንፃርም ኢትዮጵያ ይሄን ጉባኤ ለማከናወን ለህብረቱ ቃል በገባችው መሰረት በተለይ ከኮቪድ-19 ምርመራና ህክምና ጋር በተያያዘ ጥሩ ዝግጅት መደረጉ ተመላክቷል።
 
በዚህም ወደ አፍሪካ ህብረት የሚገባ ማንኛውም አካል የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤት በማሳየት በመሆኑ ይሄንን የሚመጥን ምርመራም በኤርፖርት፣ ሆቴሎችና በአፍሪካ ህብረት ግቢ እንደሚደረግ ተገልጿል።
 
ድንገተኛ ህመም ቢያጋጥምም የህክምና መስጫ ቦታ ከብቁ ባለሙያዎች ጋር መዘጋጀቱ ነው የተጠቆመው።
 
መድረኩን የመሩት የብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ÷ ሁሉም መስርያ ቤቶች ያከናወኑት ቅድመ ዝግጅት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
የቀሩ ስራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁም ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።
 
ኢትዮጵያ ይሄን አጋጣሚ በመጠቀም መልካም ገፅታዋን አጉልታ የምታሳይበት አጋጣሚ ነው ያሉት አምባሳደር ብርቱካን÷ ጉባኤውን በስኬት አስተናግዶ ለማጠናቀቅ ብርቱ ትብብርና ጠንካራ ቅንጅት ያስፈልገናል ብለዋል።
 
ጉባኤውን ለማዘጋጀት የገባናቸውን ቃልም በተግባር ለመፈፀም ስራዎች ሁሉ በጥንቃቄና በአትኩሮት መሰራት አለባቸው ሲሉ ማሳሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
Exit mobile version