አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል በመፍጠር ዙሪያ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና በኢንደስትሪው ትስስር ዙሪያ የማእድን ሚኒስቴር ያዘጋጀው ምክክር ተጀምሯል።
የዘርፉ ምሁራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች የተገኙበትን ይህንኑ ምክክር ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንግግር ከፍተዋል።
ኢንጂነር ታከለ ዘርፉ ይበልጥ እንዲጎለብት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ያለው ተስስር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
በዚሁ ምክክር ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እውቀትን ማእከል ያደረጉ ኢንደስትሪዎች በልማቱ ረገድ ሰፊ ርቀት ሊጓዙ ይችላሉ፣ የማእድን ዘርፉም ይህ እጅጉን ያስፈልገዋል ብለዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚያስመርቁት የሰው ሃይል ብዛት ሳይሆን በጥራቱና በተለየ መስክ ላይ ትኩረት አድርገው መስራታቸው ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።
ሀገሪቷ ያላትን ማእድን በቅጡ መጠቀም የምትችለው እውቀትን መሰረት ማድረግ ሲቻል ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፥ በማእድን ዘርፉ የታዩ ከተቋማቱ ጋር አብሮ የመስራት ፍላጎት በሌሎችም ዘርፎች መቀጠል አለበት ነው ያሉት።
ለዘርፉ ወሳኝ ሚና የሚኖራቸው አዳዲስ የትምህርት መስክ የመክፈትም ይሁን ያሉትን የልህቀት ማእከል የማድረግ አካሄድ የሚበረታታና መታገዝ ያለበትም መሆኑን ገልፀዋል።
በሀብታሙ ተ/ስላሴ