Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ዱቤ ባለመከፈሉ መቸገሩን መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሆስፒታሎች በዱቤ ለወሰዱት መድሃኒት መክፈል የሚገባቸውን 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ባለመክፈላቸው ስራው እንደተስተጓጎለበት የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ጤና ተቋማት በዱቤ የወሰዱት ብዙ ተሰብሳቢ ብር በመኖሩ በአቅርቦቱ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ነው ያመለከተው፡፡

ጤና ተቋማት በዱቤ የወሰዱት ተሰብሳቢ ብር በወቅቱ ገቢ ባለመሆኑ ገዝተን በምናቀርባቸው የህክምና ግብቶች ላይ በወቅቱ እና በበቂ መጠን ለማቅረብ ችግር እየተፈጠረ ነው ብለዋል የአገልግሎቱ የፋይናስ ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ሳሙኤል፡፡

ከአምስት አመት ጀምሮ በአጠቃላይ ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የዱቤ ሽያጭ ክፍያ በየሆስፒታሉና ጤና ተቋማት እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን ፥ ከፍተኛው የዱቤ ተሰብሳቢ በአዲስ አበባ በሚገኙ ጤና ተቋማት እንዳለ ገልፀዋል። እያንዳንዳቸው እስከ 85 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ተሰብሳቢ ያለባቸው ሆስፒታሎች አሉም ተብሏል፡፡

በክልል ከሚገኙ ቅርንጫፎች ባህርዳር 124 ሚሊየን ፣ አዳማ 91 ሚሊየን፣ ሀዋሳ 90 ሚሊየን ፣ ደሴና ጅማ 50 ሚሊየን ተሰብሳቢ ብር ያለባቸው ቅርጫፎች ለአብነት ተጠቃሽ መሆናቸውን አቶ ዘውዱ ተናግረዋል፡፡

የአገልግሎት ተቋሙ ፥ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለማሳለጥ የተሰብሳቢ የዱቤ ሽያጭ መኖሩ ማነቆ እንደሆነበት ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

የህክምና ግብዓቶችን ቶሎ ቶሎ በማሰራጨት ብዙ ሽያጭ እንዲኖረን እንፈልጋለን ያሉት ሀላፊው ፥ ከመንግሥት ካዝና በጀት የሚበጀትላቸው ጤና ተቋማት ያለባቸውን ብድር በወቅቱ እንዲከፍሉ አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version