Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሩዋንዳ ከ3 ዓመታት በኋላ ከኡጋንዳ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ልትከፍት ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩዋንዳ ለ3 አመታት ዘግታው የነበረውን ከኡጋንዳ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ልትከፍት መሆኑን ገለጸች፡፡
ሩዋንዳ ከኡጋንዳ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር መከፈቷ የተሰማው የኡጋንዳ ጦር አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሙሁዚ ካይኔሩጋባ ወደ ሮዋንዳ አቅንተው ከፕሬዜዳንት ፖል ካጋሜን ጋር ከመከሩ ከቀናት በኋላ ነው ተብሏል፡፡
ሩዋንዳ በፈረንጆች የካቲት 2019 ሰሜናዊ ከኡጋንዳ ጋር የሚያገናኛትን የድንበር በር በመዝጋት ዜጎች ወደ ዚያች ሀገር እንዳይጓዙ ስታስጠነቅቅ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ እና የኡጋንዳው አቻቸው ዩዌሪ ሙሴቬኒ በአንጎላ እና በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሪዎች ሸምጋይነት ቢነጋገሩም ውጥረቱ ለዓመታት ቀጥሎ ቆይቷል።
የሩዋንዳ መንግስት የህዝቦቹን ችግር ለመፍታት እና በኡጋንዳ በኩልም በሁለቱ ሀገራት ሰላም ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት ግምት ውስጥ በማስገባት የድንበሩ መከፈት መወሰኑን ዘገባው አመላክቷል፡፡
ሩዋንዳ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጠናከር መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አስታውቃለች፡፡
ኮቪድ-19ን መከላከልን በተመለከተም ሁለቱ ሀገራት በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ተገልጿል፡፡
የድንበሩ በድጋሚ መከፈት በድንበር አቋርጠው የንግድ ስራ ለሚከውኑ፤ በድንበር ዙርያ ኑሯቸውን ላደረጉ እና ለትምህርት እና ለጤና አገልግሎት ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር ለሚንቀሳቀሱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ከፍተኛ እፎይታ ይፈጥራል ነው የተባለው፡፡
ሁለቱ ሀገራት በሚዋሰኑበት ድንበር ላይ የሚገኙ ህዝቦች በደም የተሳሰሩ እና ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩም ጭምር እንደሆኑ ዘገባው ያስረዳል፡፡
በሩዋንዳ በኩል ኡጋንዳ ኪጋሊ ላይ ነፍጥ ያነሱ ቡድኖችን ትደግፋለች የሚል ክስ ሲነሳ ኡጋንዳ በፊናዋ ሩዋንዳ ግዛቴ ውስጥ ዘልቃ የስለላ ተግባር ትፈጽማለች በቁልፍ የደህንነት ኤጀንሲዎች ውስጥም ሰርጎ ለመግባት ሞክራለች ስትል ትከሳለች ብሏል የአናዶሉ ዘገባ።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version