አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት 171 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገለጸ።
ይህ የተገለፀው ሚኒስቴሩ “አገልጋይነት መገለጫችን ነው” በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው የእውቅናና የሽልማት መርሃ ግብር ላይ ነው።
የገቢዎች ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌው እንዳሉት፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በያዝነው በጀት ዓመት 364 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ ይገኛል።
በ6 ወራት ውስጥም 185 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ነው 171 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ነው የገለፁት።
በወዳጅነት አደባባይ እየተካሄደ ባለው መርሃ ግብር ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ የሁለተኛ ዙር የሰራተኛና የአመራር የእወቅናና የሽልማት ስነ ስርዓት እያከናወነ ይገኛል።
መስርያ ቤቱ በስራ አፈፃፀማቸው ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ሰራተኞችና አመራሮች እንዲሁም ተቋማት በዛሬው ዕለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት እየሸለመ ነው፡፡
የሽልማት ስነስርዓቱ በሶስት ደረጃ የተከፈለ ሲሆን ፥ የብር፣ የወርቅና የፕላቲኒየም ደረጃ ተሰጥቶት ላፕቶፕ፣ ዋንጫ እና የገንዘብ ሽልማት ተዘጋጅቷል።
በታሪኩ ለገሰ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

