አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ1 ቢሊየን 427 ሚሊየን ብር ወጪ በመገንባት ላይ የሚገኘው የባህር ዳር አባይ ወንዝ ድልድይ ፕሮጀክት ግንባታ የደረሰበት ደረጃ እና የፋይናንስ አፈጻፀም 57 በመቶ ደረሰ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የድልድይ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻፀም የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
በምልከታ ወቅት የባህር ዳር አባይ ወንዝ ድልድይ ፕሮጀክቱ ኢንጅነርና አማካሪ ሰርዳር መህመት ፥ በ1 ቢሊየን 427 ሚሊየን ብር ወጪ በመገንባት ላይ የሚገኘው ድልድይ በጣም ውስብስብ ባለ ገመድ መወጠሪያ ያለውና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ግብዓት ግንባታው እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የግንባታ ፕሮጀክቱ ሎት 1 እና ሎት 2 ተብሎ እንሚከፈል የተናገሩት አማካሪው፥ ሎት 1 የዋና ድልድይ ግንባታ ሲሆን፥ ግንባታውም እ.ኤ.አ. በ2023 እንደሚጠናቀቅ ፤ ሎት 2 ደግሞ ድልድዩን ጨምሮ 3 አደባባዮችን የሚያገናኝ 7 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአስፋልት መንገድ ግንባታ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ግንባታውም በፈረንጆቹ 2024 እንደሚጠናቀቅም ነው ያከሉት፡፡
ከምልከታው በኋላ የቡድኑ አባላት የድልድዩ ግንባታ መጓተት ምክንያቶችን፣ የፊዚካልና የፋይናንስ አፈፃጸምን፣ የዕውቀት ሽግግርና ዕሴቶችን ጨምሮ የስራ ዕድልን በመፍጠር ረገድ ፕሮጀክቱ ያለውን ፋይዳ፣ የሰራተኞች የስራ ላይ ደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች መሟላትን በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ከፕሮጀክቱ የስራ ሃላፊዎች ጋር በስፋት ተወያይተዋል፡፡
ይህ 385 ሜትር ቁመትና 49 ሜትር ስፋት ያለው፣ በግራና በቀኝ 6 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማሳለፍ የሚችለው ድልድይ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከ50 ዓመታት በላይ ያገለገለውን ነባሩን የባህር ዳር ድልድይ የመፍረስ አደጋና የትራፊክ መጨናነቅ እንደሚያስቀር ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የግንባታ ፕሮጀክቱ የፊዚካልና የፋይናንስ አፈጻፀም አሁን ላይ 57 በመቶ ላይ መድረሱ ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

