አዲስ አበባ፣ ጥር 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዘመናዊ የእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶችን በመደገፍ በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጋምቤላ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ከተሰማሩ ደንበኞቹ ጋር በጋምቤላ ከተማ ዛሬ ውይይት አካሄዷል።
የባንኩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ የግብርናው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ብዙ ለውጥ ያልመጣበት ቢሆንም በዘንድሮው ዓመት ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በተለይ ከሶስት ዓመት በፊት በባንኩ የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን በማስተካከል በዘመናዊ የእርሻ ልማት ለተሰማሩ ባለሃብቶች የብድር አገልግሎትና ሌሎች ድጋፎችን ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ባንኩ የአሰራር ክፍተቶችን በማረምና የኮርፖሬሽኑን የብድር ደንበኞች ወደ ለውጥ መስመር በማስገባቱ ባለፍው ዓመት ከ3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ጠቅሰዋል።
በጋምቤላ ከልል 154 የእርሻ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም ቀደም ሲል በነበረው የብድር አሰጣጥ ክፍተት 62ቱ ብቻ በስራ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው÷ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ተገቢ ባልሆነ መልኩ ወጪ የሆኑ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ለማስመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክትር ተገኝወርቅ ጌጡ በበኩላቸው÷ ባንኩ ግብርና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በሆነው በዘመናዊ የእርሻ ልማት ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊውን የብድር አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ ዝናብ ላይ ብቻ የተመሰረተና ዘመናዊ የግብርና አሰራር ዘይቤ ለማይከተሉ ባለሃብቶች የብድር አገልግሎት ቦርዱ መከልከሉን ነው የገለጹት።
ባንኩ ክልከላውን ያደረገው ባለፉት ዓመታት ከሰጠው ብድር ውስጥ 7 ቢሊየን ብር በማጣቱ ምክንያት እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

