አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የእናት አገራቸውን ጥሪ ተከትለው አገር ቤት ከሚገኙ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በስካይላይት ሆቴል እየመከረ ነው፡፡
በጦርነት የወደሙ ከተሞችን መልሶ በመገንባት ላይ ባተኮረው በዚህ መድረክ ላይ ሚኒስትሮችና የከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ ባለሃብቶች ተገኝተዋል፡፡
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ ‘‘በጦርነቱ ከተሞቻችን ክፉኛ ተጎድተዋል ፤ መሰረተ ልማታቸው በሙሉ ወድሟል ፤ ተዘርፏልም ፤ ከሁሉ በላይ በከተሞች የሚገኙ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ተቋማት እንዳልነበሩ ሆነዋል’’ ነው ያሉት፡፡
አክለውም፥ አሸባሪው ህወሓት በሚችለው ሁሉ መረጃዎችን የማጥፋት የጭካኔ ተግባር ፈፅሟል ፤ በተለይም የቤትና የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ዶሴዎች ወድመዋል ፤ መረጃዎቹን የያዙ ኮምፒውተሮችና የመዝገብ ማከማቻዎች ኢላማ ተደርገዋልም ነው ያሉት፡፡
‘’ከተሞችን መልሶ ለማቆም በተጀመረው በዚህ ታላቅ ዓላማና ኃላፊነት ውስጥ የእናንተ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች እጆችን የግድ የሚሉ በርካታ ቀዳዳዎች አሉ’’ ሲሉ ለዳያስፖራው ማህበረሰብ አስረድተዋል ሚኒስትሯ፡፡
‘‘አገራችሁን በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጋችሁ እንዳኮራችሁና አሸናፊ እንድትሆንም በዓለም ፊት እንደጮሃችሁት ሁሉ በዚህ መልሶ ቀና የማድረግ ሥራ ውስጥም አብረን ተባብረን የጦርነት ጠባሳችንን እንድንጠግን ጥሪዬን አስተላልፋለሁ’’ ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

