አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተደጋጋሚ የደህንነት ማረጋገጪያ ካገኘና ሁለቴ የበረራ ሙከራ ካደረገ በኋላ በዛሬው እለት ይፋዊ የበረራ ማስጀመር መርሃ ግብሩ አካሄዷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከመከስከሱ ከወራት በፊት ተመሳሳይ አውሮፕላን ኢንዶኔዢያ ውስጥ ተከስክሶ ነበር።
ከተደጋጋሚ አደጋ በኋላ በመላው ዓለም የሚገኙ አየር መንገዶች አሜሪካ ሠራሹን አውሮፕላን ቦይንግ 737 ማክስን ማብረር አቁመው ነበር።
ቦይንግ ኩባንያ በአውሮፕላኑ መሳሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ምርመራና ፍተሻ ካደረገ በኋላ ለአደጋው መንስኤ ናቸው የተባሉ የበረራ መሳሪያዎችን ማሻሻሉን ወይንም ማስተካከሉን አስታውቋል።
የፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን /FAA/፣ የአውሮፓ ህብረት የአቪየሽን ደህንነት ኤጀንሲ /EASA/፣ ትራንስፖርት ካናዳ፣ የቻይና ሲቪል አቪየሽን አስተዳደር /CAAC/፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን /ECAA/ እንዲሁም ሌሎች የአቪየሽን ተቆጣጣሪ አካላት ለአውሮፕላኑ ምስክርነትና ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
በዚህም 36 የሚሆኑ የአለም አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ወደ አገልግሎት መልሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም ተደጋጋሚ የደሕንነት ማረጋገጪ ካገኘና ሁለቴ የበረራ ሙከራ ካደረገ በኋላ በዛሬው እለት ይፋዊ የበረራ ማስጀመር መርሃ ግብሩን አካሄዷል።
በዚሁ ወቅት አቶ ተወልደ ገብረማርያም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ወደ አገልግሎት መመለስ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት “የበረራ ደህንነት የአየር መንገዳችን ተቀዳሚና ወሳኝ ጉዳይ ነው፤ እያንዳንዷ የምንሰራት ስራና የምንወስናት ውሳኔ በበረራ ደህንነት አብይ ጉዳይ የተቃኘ ነው” ብለዋል።
“በዚህ መርህ ላይ በመመስረት ነው ዛሬ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላናችንን ወደ አገልግሎት የመለስነውም” ነው ያሉት።
የማክስ አውሮፕላን ሞዴል ዳግም ወደ በረራ ከተመለሰበት አንድ ዓመት ወዲህ በአጠቃላይ 349 ሺህ በረራዎችን ያደረገ ሲሆን፥ በዚህም ወደ 900 ሺህ የሚደርስ የበረራ ሰአት አስመዝግቧል።
በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ፣ የአየር መንገዱ የማኔጅመንት አባላት፣ የቦይንግ የስራ ኃላፊዎች፣ ሚኒስትሮች፣አምባሳደሮች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ደንበኞች በዚህ የመጀመሪያ በረራ ላይ ተገኝተዋል።
በሸዋ ማስረሻ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

