በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስን በተመለከተ በ6 ወር ብቻ 32 ሚሊየን 953 ሺህ 596 ብር ለመንግስት ገቢ መደረጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
ከመሬት ጋር በተያያዘም 2 ሺህ የሚሆን ካሬ እንዲወረስ ውሳኔ አግኝቶ መሬቱ ወደ መሬት ባንክ በመግባት ሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በግማሽ አመቱ በተለያዩ ንብረቶች ላይ እግድ እንዲጣል ተደርጓል።
በዚሁ መሠረትም ስምንት ድርጅቶች በገንዘብ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን 406 ብር፣ በሼር 32 ሚሊየን 516 ሺህ ብር፣ በተሽከርካሪ 233፣ በቤት 80 እና ማሽነሪ 114 ላይ እግድ ተጥሏል ፡፡
ከድርድር አፈጻጸም ጋር ተያይዞ በግማሽ አመቱ 25 መዛግብት ለድርድር ቀርበው ሁለት መዛግብት በስኬት መጠናቀቃቸው የተገለጸ ሲሆን፥ መዛግብቱ የያዙት የገንዘብ መጠንም አንደኛው 59 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ሲሆን÷ ሁለተኛው 87 ሺህ 494 የአሜሪካ ዶላር ነው ተብሏል፡፡
የግልግል ዳኝነት አፈጻጸም በሚመለከት በቀረበው ሪፖርት ከ11 ጉዳዮች በአንደኛው መዝገብ ኢትዮጵያ ከቀረበባት ክስ ነጻ መውጣቷ በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህም የ300 ሚሊየን ዶላር መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በአሸባሪው ህወሓት ምክንያት በአማራ እና አፋር ክልሎች የተፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያጣራ የምርመራ ቡድን በሁሉም ቦታዎች የወንጀል ምርመራ በማድረግ የተፈጸሙ ወንጀሎችን፣ ወንጀል ፈጻሚዎችን እና የወንጀሉን አፈጻጸም የማጣራት ስራ በመስራት የወንጀል ፈጻሚዎችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡
በሀይለየሱስ ስዩም

