Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጢስ አባይ 2 ኃይል ማመንጫ አንድ ዩኒት ተጠግኖ ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከስምንት ዓመታት በላይ በብልሽት ምክንያት የቆመው የጢስ አባይ 2 የውሃ ኃይል ማመንጫ አንድ ዩኒት ሥራ ጥገና ተጠናቆ 25 ሜጋ ዋት ኢነርጂ ማምረት መጀመሩን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ጉታ አስታወቁ፡፡

ኃላፊው እንደገለፁት ÷የዩኒቱ ውሃ መውጫ በደለል ስለተሞላና የተርባይን ሻፍት ዝንፈት በማጋጠሙ ዩኒቱ ከስምንት ዓመታት በላይ ሥራ አቁሞ የነበረ ሲሆን÷የተቋሙ ሠራተኞች በራስ ተነሳሽነት ሥራውን መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የጥገና ቡድኑ መሪና የፊንጫ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሹመት በላቸው በበኩላቸው÷ የጥገና ሥራው ከተጀመረ በኋላ የተርባይን ሻፍት ዝንፈትን የማስተካከል፣ ዩኒቱ እንዲሰራ ለማድረግ ተሸከርካሪ አካሉን ወይም ሮተር ከፍ የማድረግ ፣ የተርባይኑን ተሸከርካሪ አካል የማስተካከል ሥራዎች ፣ የአውቶማቲክ የቮልቴጅ መቆጣጠሪያ ሥራዎች እና ሌሎች ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል፡፡

ጠላቂ ዋናተኞችን በመጠቀምም የተቀረቀረን የድራፍት ቱብ በር የማውጣት ሥራዎች መሰራታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

በትናንትናው ዕለትም 25 ሜጋ ዋት እንዲጭን በማድረግ ሥራው በስኬት መጠናቀቁን ገልፀው የተጠገነው ዩኒት በሙሉ አቅሙ 30 ሜጋ ዋት መጫን እንደሚችል አቶ ሹመት አስታውቀዋል፡፡

የጢስ አባይ 2 የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሥራ የጀመረው በ1993 ሲሆን÷ 72 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ ጣቢያ ነው፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version