Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአፍሪካ ሰላም እና ልማት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል – ሙሳ ፋኪ ማህመት

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአፍሪካ ሰላም እና ልማት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት ገለፁ።
ሊቀመንበሩ በ35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በተለያዩ የአህጉሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የሰላም መደፍረስ ችግሮችን ለማስወገድ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አፍሪካ ሙስናን እና የስልጣን መባለግን የመሳሰሉ ችግሮችን በመዋጋት አጀንዳ 2063ን ለማሳካት መስራት እንደሚገባትም ነው የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳፋቂ የተናገሩት፡፡በአፍሪካ አገራት መካከልም የተጠናከረ ትብብር እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የለውጥ መርሃ ግብር የውስጥ አቅምን ማሳደግ በሚቻልበት መልኩ ተጠናክሮ ሊቀጠል እንደሚገባ ጠቁመው፥ አህጉር በቀል ሃብቶችን ማሰባሰብ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ጉባኤው “የአፍሪካ አኅጉርን የሥርዓተ ምግብ አቅም በመገንባት፤ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማትን ያፋጥናል” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ እና ነገ የሚካሄድ ይሆናል።
በተመሳሳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ በ35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ መላው አለም አፍሪካ ኮቪድን ለመቆጠጠር እያደረገች ያለውን ጥረት እንዲያግዝ ጠይቀዋል።
የኮቪድ ክትባትን አህጉሪቱ በራሷ አቅም ለማምረት የጀመረችው ጥረት ሊበረታታ እንደሚገባው የገለጹት ዋና ጸሀፊው፥ ደቡብ አፍሪካ ክትባቱን ለማምረት የጀመረችውን ጥረት አድንቀዋል፡፡
በተያያዘም ለአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ፣ የጾታ እኩልነት እና ስራ ፈጠራ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ነው አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጉባኤው ባስተላለፉት መልዕክት የተናገሩት፡፡
በኮቪድ የተጎዳው የአፍሪካ ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠቁመው፥ የተለያዩ አገራት እና አለም አቀፍ ድርጅቶች ቃል የገቡትን የገንዘብ ድጋፍ ተፈጻሚ ያደርጉ ዘንድ አሳስበዋል።
በወንደሰን አረጋኸኝ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version