Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የጤናማ እናትነት ወርን በተለያዩ ዝግጅቶች አከበረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ በሀገራችን ለ16ኛ ጊዜ የሚከበረውን የጤናማ እናትነት ወርን በተለያዩ ዝግጅቶች ሲያከብር ውሏል።

የማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ አበበ ሽብሩ ÷ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ያለው የጤናማ እናትነት ወር ሁላችንም ለእናቶች ጤና ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን መንቀሳቀስ እንዳለብን የሚያመለክት ነው ብለዋል፡፡

ማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ፥ ከጥር 23 ጀምሮ እስከ ጥር 27/ 2014 ለአንድ ሣምንት በቆየ መርሃ ግብሩ ዘመናዊ አልትራሳውንድን ጨምሮ ሌሎች የሕክምና መሳሪያዎችን ይዞ በመንቀሳቀስ በአዲስ አበባ ÷ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ- መሿለኪያ ጤና ጣቢያ፣ ከቸርችል ጤና ጣቢያ እንዲሁም ከጃንሜዳና ከአዲሱ ገበያ ጤና ጣቢያዎች ጋር በመተባበር የረጅም ጊዜ ልምድ ባላቸው የማህጸን እና ጽንስ እንዲሁም የራዲዎሎጂ ስፔሻሊስት ሐኪሞችን ለ381 እናቶች ነጻ የጤና ምርመራ አገልግሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል ነው የተባለው።

በመርሃ ግብሩ በተለይም የመክፈል አቅም በማጣት ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ ነፍሰ ጡር እናቶች አገልግሎቱን በነጻ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በዛሬው ዕለትም በጎተራና በአራዳ የእናቶችና ህጻናት ልዩ ማዕከል የደም ልገሳ መርሀ ግብር ሲካሄድ ውሏል።

በሌላ በኩል ጤና ሚኒስቴር ÷ በአፋር እና በደሴ ከተሞች ባከበረው የጤናማ እናትነት ዝግጅት ላይ በድምሩ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የሕክምና ግብአቶችን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን በሥርዓተ ጾታ እና ተዋልዶ ላይ ከሚሰራው “UNFPA” ጋር በመተባበር ጉዳት ለደረሰባቸው የሕክምና ተቋማት ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን አሳይቷል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version