Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

489 ወጣቶችን የሥራ ልምምድ ለማስጀመር የመጀመሪያው ዙር የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል መንግስት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በከተሞች የምግብ ዋስትና እና የሥራ ፕሮጀክት የተዘጋጀ የሥራ ልምምድ የመጀመሪያ ዙር ፕሮግራም 489 ወጣቶች ለ10 ቀን የሕይወት ክህሎት ማጎልበቻ ሥልጠና በመስጠት ተጠናቋል፡፡

ፕሮጀክቱ ትምህርታቸውን በተለያየ ምክንያቶች ባቋረጡ እና ሥራ በሌላቸው ወጣቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን ከሠልጣኞቹ 60 ከመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ 102ቱ ህፃናት ልጆች ያላቸው ናቸው፡፡

በማጠናቀቂያ ሥልጠናው ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሥራ ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ÷ ወጣቶቹ በሥራ ልምምድ ወቅት የኪስ ገንዘብ እየተሰጣቸው ቆይተው ብቁ ከሆኑ እንደሚቀጠሩ ገልጸዋል፡፡

ይህን ዕድል ከመጠቀም አኳያ በሂደት የሚገጥሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው፣ የኢንዱስትሪውን ህግና ስርዓት ጠብቀው መሥራትና መለማመድ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከ700 በላይ ወጣቶችን ሥራ ለማለማመድ 99 የግል ድርጅቶች ፈቃደኛ በመሆናቸው በመንግስትና በስልጣኞች ስም ያመሰገኑት አቶ ንጉሡ÷ ወጣቶቹም ልምምዳቸውን በሚገባ በማጠናቀቅ ለሌሎች ወንድም እና እህቶቻቸው ፈር ቀዳጅ መሆን እንደሚገባቸው ምክራቸውን ለግሠዋል፡፡

በልምምድ ወቅትም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከጎናቸው መሆኑን በማረጋገጥ ለስልጠናው የተባበሩትን ሁሉ አመስግነው የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሥልጠናው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በ11 ከተሞች 70 ሺህ ወጣቶችን አሠልጥኖ የሥራ ዕድል ለማመቻቸት የተቀረፀ ፕሮጀክት አካል እንደሆነና በአዲሰ አበባ ብቻ ለ49 ሺህ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version